ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ነጥብ ተጋርተዋል

በአዲስ አበባ ስታድየም የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ጨዋታ በግንባር በተቆጠሩ ጎሎች በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

መከላከያ አዳማ ላይ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ቴዎድሮስ ታፈሰን አሳርፎ ፍፁም ገብረማርያምን ያስገባበትን ለውጥ ሲይደርግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ያለግብ ከተጠናቀቀው የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ሀምፍሬይ ሚዬኖ እና አቤል ያለውን በናትናኤል ዘለቀ እና በኃይሉ አሰፋ ተክቷል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። 3ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከአስቻለው ታመነ ከነጠቀውን ኳስ ፓትሪክ ማታሲ የግብ ክልሉን ሳይሸፍን በፊት ሳሙኤል ታዬ ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት ኳስም የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሆኗል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከርቀት የሞከረው ኳስ ለጥቂት ነበር ወደ ላይ የተነሳው። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው መከላከያዎች ፍፁም ገብረማርያም በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በቀኙ የአብዱልከሪም እና አሜ መሀመድ የሜዳው ቁመት ጥምረት ላይ አመዝነው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ጨዋታው በተለይም እስከ 25ኛው ደቂቃ ድረስ ጠንካራ ሙከራዎች ሳይደረጉበት የዘለቀ ነበር።

በተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ከፊት ያሉ ተጫዋቾችን ከግብ ጠባቂ ጋር ለማገናኘት ይሞክሩ የነበሩት መከላከያዎች ባልተመጠኑ ቅብብሎች እና በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በሆነ እንቅስቃሴያቸው ሳቢያ ጥረታቸው ኬኒያዊውን ግብ ጠባቂ መፈተን ሳይችል ቀርቷል። መሀል ላይ ከታደለ መንገሻ እንቅስቃሴ መነሻነት በቶሎ ወደ ጦሩ የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም የተጋጣሚያቸው የተከላካይ መስመር በፍጥነት እያገገመ ክፍተቶችን በመሸፈን ኳሶችን እያስጣላቸው አደገኛ ሙከራ እንዳያደርጉ አግዷቸዋል።

ጨዋታው ሞቅ ባለባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ግን ከሁለቱም ቡድኖች እጅግ አደገኛ ሙከራዎች ተደርገዋል። በመከላከያ በኩል 26ኛው ደቂቃ መሀል ላይ ከጥሩ ንክኪዎች ያገኘውን ኳስ በቀኝ በኩል ይዞ በመግባት ፍፁም ገብረማርያም አክርሮ ሲሞክር ማታሲ አድኖበታል። ፍፁም የተደረበውን ኳስ በድጋሜ ከቅርብ ርቀት አክርሮ የመምታት ዕድልን ቢያገኝም አሁንም ማታሲ አውጥቶበታል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አማኑኤል ተሾመ በስህተት ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ ሪቻርድ አርተር በግራ በኩል ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ አክርሮ ቢመታም አቤል ማሞ ሊያወጣበት ችሏል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን ፍሩምፖንግ ሜንሱ ከመሀል ሜዳው የግራ ወገን በረጅሙ የላከው ኳስ በአብዱልከሪም መሀመድ ከቀኝ ሲሻማ አሜ መሀመድ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎችም ጥሩ ፉክክር የታየባቸው ሆነው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 መሪነት ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ መከላከያዎች ከቆሙ ኳሶች ጫና መፍጠር ችለዋል። ዳዊት እስጢፋኖስን ቀይሮ የገባው ቴዎድሮስ ታፈሰ 46ኛው ደቂቃ ላይ ያሻማውን ወደ ግራ ያደላ የርቀት ቅጣት ምት አዲሱ ተስፋዬ በግንባሩ ሲገጭ ኳሱ ተጨርፎ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ላይ ወጥቷል። በዛው ደቂቃ ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችን ቢያገኙም መከላከያዎች ተጫማሪ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም። ከዚህ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ታይቷል። መሀል ላይ ተረጋግተው ኳስ መቆጣጠር ያልቻሉት መከላከያዎች ከሜዳው አጋማሽ ካለፉ በኋላ እንቅስቃሴያቸው በቀላሉ ሲኪስም ይታይ ነበር። በተሻለ ወደ ፊት ገፍተው ይጫወቱ የነበሩት ጊዮርጊሶችም ወደ ጦሩ የግብ ክልል በሚጠጉባቸው አጋጣሚዎች ኳሶችን ወደ መስመር በማውጣት ቢጠመዱም የወትሮው ተሻጋሪ ኳሶቻቸው ሊታዩ አልቻሉም። 75ኛው ደቂቃ ላይ በአዲሱ እና አማኑኤል አለመናበብ ምክንያት በግራ መስመር በኃይሉ አሰፋ ነፃ ሆኖ ያሻማውን ኳስ ሦስት የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከቅርብ ርቀት ለመግጨት ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካ የቀረበት ቅፅበት ብቻ ነበር ሊጠቀስ የሚችለው።

ጨዋታው በተቀዛቀዘ መንፈስ ቀጥሎ 83ኛው ደቂቃ ላይ ከብዙ ቆይታ በኋላ ሳጥን ውስጥ የተገኙት መከላከያዎች የአቻነቷን ግብ አግኝተዋል። ፍሬው ሰለሞን ያሳለፈለትን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ በቀኝ በኩል ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ ወደ ውስጥ ሲያሻማ በፍፁም ቦታ የገባው ተመስገን ገብረኪዳን በግንባሩ በግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የተሻለ ፍጥነት ቢታይበትም ቡድኖቹ በረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ አልሆነም። የተሻለ አስፈሪነት የነበራቸው መከላከያዎች በጭማሪ ደቂቃ ፍቃዱ እና ፍሬው ሳጥን ውስጥ በቅብብል በፈጠሩት ዕድል ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም ሳይሳካላቸው ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡