የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው የዛሬው የመከላከያ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

“በውጤቱ ብዙ አልተከፋሁም” በለጠ ገብረኪዳን – መከላከያ

ስለጨዋታው

“ቡድናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና ከነበረበት ችግርም ወጥቶ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ተመርቶ አቻ መውጣቱ ራሱ ጥሩ ነው። ጊዮርጊስ ትልቅ ቡድን ከመሆኑም አንፃር ውጤቱን አልተከፋንበትም። ያለንበት ነገር አስቸጋሪ በመሆኑ ሦስት ነጥብ ማግኘት አለብን ብለን ነበር የተጫወትነው። ከዛ አንፃር ትንሽ ተከፋን እንጂ ጥሩ የግብ ዕድሎችንም አግኝተን ነበር። እነዛን ብንጠቀም ደግሞ ከዚህ የተሻለ ውጤትም ይዘን እንወጣ ነበር። በውጤቱ ብዙ አልተከፋውም ፤ ተጫዋቾቼ በከፈሉት መስዕዋትነትም ደስተኛ ነኝ።”

ቅያሪዎችን በተመለከተ

“አሰላለፋችንን እከመጨረሻው አልቀየርንም ፤ በሦስት አጥቂ ነው የተጫወትነው። ነገር ግን መጀመሪያ ካመከናቸው ኳሶች አንፃር ቅያሪ አድርገናል። ተቀይሮ የገባው ተጫዋችም ነው ግብ ያስቆጠረው። ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ግብ የሚያስቆጥር ተጨዋች መኖሩ ደግሞ ለበድኑ ጥሩ ነገር ነው።”

“ጨዋታውን ብዙ መጥፎ ነገር አላየሁበትም” ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“ጨዋታውን ብዙ መጥፎ ነገር አላየሁበትም ። ግን የተጫዋቾቻችንን ሥነ ልቡና ለመገንባት የሚጠቅመን ጨዋታ ነበር ሳይሳካ አቻ ወጥተናል።”

በድኑ ነጥብ የመጣሉ ምክንያት

“ሁለተኛ እና ሦስተኛ ግብ ለማግባት ጉጉት ስለነበረብን መስመሮች ላይ በፈጠርነው ክፍተት ግብ ተቆጥሮብን ዕኩል ለመውጣት ተገደናል እንጂ የሚገባን አይደለም ፤ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት በምንሞክርበት ሰዓት የተቆጠረብን ከመሆኑ አንፃር ማለት ነው። ሆኖም እግር ኳስ ነው እና ያጋጥማል።”

ከጉዳት ስለተመለሱ ተጫዋቾች

“ከዚህ በፊት በነበረው ጨዋታ አቤልን በጉዳት አጥተናል። ናትናኤል እና ምንተስኖት ደግሞ ከጉዳት ተመልሰው የተሻለ ነገር እንዲያደርጉ የተሻለ ደቂቃዎችን ሰጥተናቸው ነበር ፤ ያው ውጤቱን መቀየር አልተቻለም። የተጫዋቾቻችን በራስ መተማመንም ወርዷል። በቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን እንዲያስተካክሉ ማድረግ ነው የሚኖርብን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡