ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

የድሬዳዋ እና አዳማን የነገ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን አንደሚከተለው አንስተናል።

ድሬዳዋ ላይ ሁለቱን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ለመጠጋት የሚደረግ ፉክክር እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል። በአንድ ነጥብ ልዩነት 10ኛ እና 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ እና አዳማ በወራጅ ቀጠናው ፉክክር ውስጥ ናቸው ማለት ባይቻልም ነጥባቸውን ከፍ ማድረግ ግን በሊጉ በመቆየታቸው ጉዳይ ይበልጥ እርግጠኛ የሚያደርጋቸው ይሆናል።

በሜዳቸው ያደረጓቸውን የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች በድል የተወጡት ድሬዎች ሳምንት በባህር ዳር ቢሸነፉም የሁለተኛው ዙር መሻሻላቸውን መካድ አይቻልም። በነገው ጨዋታ ግን ጉዳት ላይ ከሰነበተው ራምኬል ሎክ በተጨማሪ ናሚቢያዊው አጥቂያቸው ኢታሙና ኬይሙኒንም በጉዳት ማጣታቸው የተሻለ ግምትን ባገኙበት ጨዋታ የማጥቃት ኃይላቸውን እንዳይቀንሰው ያሰጋል። ሆኖም ድንገተኛ ቀጥተኛ ኳሶቻቸው እና ከቆሙ ኳሶች የሚፈጥሯቸው ዕድሎች ውጤታማ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።

ከሜዳ ውጪ እጅግ ደካማ ውጤት ያለው አዳማ ከተማ ከመከላከያ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ነው ለዚህ ጨዋታ የደረሰው። በሁለተኛው ዙር ብቻ አምስት ሽንፈቶችን ያስተናገደው ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ 13 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ማሸነፉ ሲታይ በወራጅ ቀጠና ውስጥ አለመገኘቱ በራሱ ጥሩ ነው። ከአንዳርጋቸው ይላቅ እና ዳዋ ሆቴሳ ጉዳት በተጨማሪ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ከነዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታ ላይ ባስተላለፈው የዲስፕሊን እርምጃ ምክንያት የመጀመሪያ አሰላለፉ ላይ በርካታ ለውጦችን ማድረግ የሚጠበቅበት ቡድኑ ጥንቃቄ ተኮር አቀራረብ እንደሚኖረው ይገመታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ ስምንት ጨዋታዎችን በድል አጠናቋል ፤ ድሬዳዋ አራቱን አሸንፏል። 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 16 ፣ ድሬዳዋ 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ 12 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት የሽንፈት ፣ ስድስት የድል ፣ ሁለት ደግሞ የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

– አዳማ ከተማ እስካሁን ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች መከላከያን ከረታበት ውጪ ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ አምስቴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ዳኛ

– ጨዋታው በተከተል ተሾመ የመሀል ዳኝነት ይመራል። አርቢትሩ እስካሁን ሦስት ጨዋታዎች ላይ የዳኘ ሲሆን ዘጠኝ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዞ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ተስፋዬ በቀለ

ብሩክ ቃልቦሬ – ኢስኤል ሳንጋሪ

ኤፍሬም ዘካርያስ – አዲስ ህንፃ – ቡልቻ ሹራ

ሙሉቀን ታሪኩ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ዘነበ ከበደ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ሚኪያስ ግርማ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ምንያህል ተሾመ – ረመዳን ናስር

ሀብታሙ ወልዴ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡