የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-0 ወልዋሎ

በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የተከናወነው የባህር ዳር ከተማ እና የወልዋሎ ዓ/ዩኒቨርስቲ ጨዋታ 0-0 ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን ብለዋል።

“ውጤቱ የሚያስከፋ አይደለም።” ሚሊዮን ታዬ (ምክትል አሰልጣኝ) – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው የደረጃ ለውጥ ስለሚያመጣ ሁለታችንም በጥንቃቄ ነበር ያከናወነው። ወልዋሎዎች በጣም የተደራጀ ቡድን ነው ያላቸው። ያንን ለመለየት 15 እና 20 ደቂቃዎችን ማጥናት ነበረብን። በዛ ሰዓት ደግሞ እነሱ በልጠውን ነበር። ነገር ግን ከዛ በኋላ ያሉ ነገሮችን ለማስተካከል ሞክረናል።

ስለ ውጤቱ

ውጤቱ የሚያስከፋ አይደለም። በደጋፊያችን ፊት ብንጫወት ጫናዎች ነበሩብን። ምክንያቱ ደረጃችንን ለማስጠበቅ ፈልገን ስለነበረ ነው። በቀጣይ ከፋሲሉ ጨዋታ በኋላ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በሜዳችን እናደርጋለን። እነሱን በማሸነፍ በሜዳችን ያለንን ነገር እናስተካክላለን።

ስለ ቡድኑ የብቃት መውረድ

ልክ ነው እየተዳከምን ነው የመጣነው። ከመጀመሪያ ጀምሮ እናውራ ከተባለ ብዙ ነገሮችን ልንዘረዝር እንችላለን። ነገር ግን የውድድሩ ጅማሮ ላይ የነበሩ ነገሮች ዋጋ አስከፍለውናል። ምክንያቱም ተገቢውን ዝግጅት ሳናደርግ ነው በቀጥታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የገባነው። ይህ ደግሞ በሁለተኛው ዙር ፈትኖናል። ከዚህ በተጨማሪ የተጨዋቾች ጉዳት ፈተና ሆኖብናል።

“ጨዋታው ማራኪ አልነበረም።” ዮሐንስ ሳህሌ – ወልዋሎ ዓ/ዩ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው የመሐል ሜዳ ጨዋታ ነው የሚመስለው። በሁለታችንም በኩል አደገኛ የሚባሉ ሙከራዎች አልነበሩም። አፈወርቅ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከሳተው ኳስ በስተቀር። በአጠቃላይ ግን የስፖርት ቤተሰብን ያላዝናና ጨዋታ ነበር። እንደ ኔ ሁለታችንም ለዋንጫም ላለመውረድም ስለማንጫወት ማራኪ ጨዋታ አላሳየንም ብዬ አስባለው።

ስለ ሁለተኛው አጋማሽ ብቃታቸው

በጨዋታው ከእረፍት በፊት እኛ የተሻልን ነበርን። ከእረፍት በኋላ ደግሞ እነሱ የተሻሉ ሆኑ። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ተጨዋቾቼ የትኩረት ማነስ ችግር ነበረባቸው። የሆነው ሆኖ እነሱ የተሻሉ የነበሩት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ላይ ነበር። ከዛ እኛ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን እና በባህር ዳር ስለነበራቸው ቆይታ

የባህር ዳር ቡድንን ከዚህ በፊት አላቀውም። በዓመቱ ውስጥ ስመለከተው የመጀመሪያ ጨዋታዬ ነው። ይህ ደግሞ በተወሰነ መልኩ ጎድቶኛል ብዬ አስባለው። ነገር ግን ከዚህ ቀደም አይቼው ስለማላውቅ መገምገም ይከብደኛል። እዚህ የነበረን ቆይታን በተመለከተ ጥሩ ነበር። እዚህ ከመጣን ምንም አይነት ችግር አላጋጠመንም። ተጨዋቾቹም በነፃነት ከህዝቡ ጋር ነበር ሲንቀሳቀሱ የነበረው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: