የአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች ውድድር 16ኛ ሳምንት ውሎ

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች 16ኛ ሳምንት ተጠባቂ አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ መድን ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አፍሮ ፅዮን ድል ቀንቷቸዋል።

አካዳሚ ሜዳ 03:00 ላይ ኢትዮጵያ መድን ከ ኢ/ወ/ስ አካዳሚ ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ሁለት ለዜሮ መመራት ተነስቶ 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አግኝቷል። እጅግ ጠንካራ ፉክክር ከጎል ሙከራ ጋር ታጅቦ በተካሄደው በዚህ ጨዋታ በሁለቱም በኩል ፍሰት ያለው እግርኳስ ከድንቅ ጎሎች ጋር አስመልክቶናል። ጎል በማግባት ቀዳሚ የነበሩት አካዳሚዎች ነበሩ። ከሳጥን ውጭ በግራ መስመር የተሰጠውን ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ናትናኤል ፍትዊ በቀጥታ ወደ ጎል ቀይሮታል። ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታ አካዳሚዎች የመጀመርያ ጎላቸውን ካስቆጠሩ ከሁለት ደቂቃ በኃላ በመልሶ ማጥቃት በአስገራሚ ፍጥነት በአንድ ሁለት ቅበብል ወደ መድን የግብ ክልል በመግባት የመጀመርያውን ጎል ባስቆጠረው ናትናኤል ፍትዊ አማካኝነት ሁለተኛ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። መድኖች በደቂቃዎች ልዩነት በተከታታይ ሁለት ጎል ቢቆጠርባቸውም ወደ ጨዋታው በፍጥነት ለመመለስ በእንቅስቃሴ ጥሩ ያልነበሩትን ሁለት ተጫዋቾቻቸውን አሰልጣኝ እንድርያስ በቀየር የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ አካዳሚዎች ተዳክመው ሲቀርቡ መድኖች በፍፁም የበላይነት አጥቅተው መጫወታቸው ሰምሮላቸው የአካዳሚው ግብ ጠባቂ ቢላል ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ሲተፋ ሀምዱ ሀሰን አግኝቶ የመድኖችን የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል። በዚች ጎል የተነቃቁት መድኖች ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ተጭነው የተጫወቱ ቢሆንም የአካዳሚዎችን የማሸነፍ ተስፋ የሚያለመልም ነፃ የጎል አጋጣሚ ከድር ዓሊ ሳይጠቀምበት መቅረቱ የቡድኑን እንቅስቃሴ አውርዶታል። በአንፃሩ መድኖች በቀሩት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብልጫ ወስደው በመጫወት ተቀይሮ የገባው ግሩም ኃ/ማርያም ከርቀት አስደናቂ ጎል አስቆጥሮ መድኖችን ሁለት አቻ ማድረግ ችሏል። ወደ ዋንጫው የሚያደርጉትን ግስጋሴ ለማጠናከር በዚህ ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት በፍላጎት ሲጫወቱ የነበሩት መድኖች በመጨረሻው ደቂቃ ከሁለት ለዜሮ መመራት ተነስተው ውጤቱን ቀልብሰው ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ያገኙበትን ጎል ግሩም ኃ/ማርያም ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ወሳኝ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 3-2 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በአካዳሚ በኩል የእግራ እግር ተጫዋች የሆነውና በአማካይ ስፍራ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው ናትናኤል ኪሮስ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ሆኖ ያገኘነው ሲሆን የኢትዮጵያ መንድ የኃላ ደጀን መሆኑን በየጨዋታዎቹ እያሳየ የሚገኘው ወደፊት ትልቅ ተጫዋች የመሆን ተስፋ ያለው አቤል ትዕግስቱ ተጠቃሽ ተጫዋች ነው።

በመቀጠል የተካሄደው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመሐል ሜዳ ላይ በተገደበ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን እንዳንመለከት አድርጎናል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ መድንን እግር በእግር እየተከተሉ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። አዳማዎች እስከዛሬ ካደረጉት እንቅስቃሴ ደከም ብለው ቢቀርቡም የኤሌክትሪኮች ተከላካይ ናትናኤል ደበላ በእራሱ ጎል ላይ በማስቆጠሩ ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ኤሌክትሪኮች ተቀይሮ በገባው በረከት ብርሀኔ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ቻሉ። ወደ ጨዋታው ለመመለስ እንዳደረጉት ጥረት ጎል ማስቆጠር የነበረባቸው ኤሌክትሪኮች በተካልኝ ኃ/ሦላሴ የግራ እግር ግሩም ጎል አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው መምራት ችለዋል። በቀሩት ደቂቃዎች ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኃላ አፈግፍገው የተጫወቱት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ያሰቡት ተሳክቶ ጨዋታውን ከመመራት ተነስተው 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።

የቀድሞ የአዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ድንቅ አጥቂ ብርሃኑ ቃሲም በዛሬው የአዳማ ጨዋታ ላይ ከአሰልጣኞች ጋር አብሮ የተመከተ ሲሆን ምናልባትም ወደፊት በአዳማ የታዳጊ ቡድኖች ውስጥ በአሰልጣኝነቱ ብቅ እንደሚል ምልክት የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን 2-1 በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ሲቀርብ በውጤት ማጣት ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ሀሌታን 2-0 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። ሌላኛው የአፍሮ ፅዮን እና የሠላም ጨዋታ ደግሞ በአፍሮ ፅዮን 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡