ሪፖርት| በከፍተኛ ውጥረት የታጀበው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐግብር በበርካታ የሜዳ ውጭ ሁነቶች ሲንከባለል ቆይቶ ለአራት ያኽል ጊዜያት የጨዋታ ቀን ለውጥ የተደረገበት የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በዛሬው እለት ከ16 ቀናት በኃላ በአዲስአበባ ስታዲየም ተካሂዶ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በከፍተኛ ውጥረት ታጅቦ በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ለወትሮው ከሚጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ላይ የተጫዋች እንዲሁም የሚና ለውጦችም በማድረግ ነበር ጨዋታው ጅማሮውን ያደረገው፡፡

በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ፍፁም በማጥቃት ቅኝት ውስጥ ሆነው ነበረው ያሳለፉት በፍጥነት ኳሶች ወደ ፊት በረጃጅሙ በመጣል ጥቃት ለመሰንዘር የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ምንም እንኳን በሙከራ ባይታጀብም በፍጥነት ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

በዚህም የተነሳ መቐለ 70 እንደርታዎች በመጀመሪያው 10ደቂቃዎች በሁለት አጋጣሚዎች የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በማጥቃት ላይ በመጠመዳቸው በተገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም በ3ኛው ደቂቃ ኦሲይ ማውሊ ከሀይደር ሸረፉ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በተዘናጉበት አጋጣሚ ያገኘውን ኳስ ከኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ወንድወሠን አሸናፊ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ በጣም አስቆጪ ሙከራ ነበር፡፡

ከፍተኛ የሆነ እልህ ይስተዋልበት የነበረው የጨዋታው የመጀመሪያ ክፍለጊዜ ከሜዳው ጭቃማነት ጋር ተደምሞሮ የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች በኩል አላስፈላጊ የሆኑ የኃይል አጨዋቶች ተስተውለዋል፡፡ ከጨዋታው አስፈላጊነት የተነሳም በጨዋታው የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች የጨዋታውን ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰን ውሳኔ በመቃወም በተደጋጋሚ ዳኛውን ሲያዋክቡ ተመልክተናል፡፡ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል አቡበከር ናስር በ12ኛው ደቂቃ አከታትሎ ከመቀሌ ሳጥን ጠርዝ ላይ የሞከራቸውና ፊሊፕ ኦቮኖ ያዳነበት ሁለት ግሩም ኳሶች ይጠቀሳሉ፡፡

እምብዛም ሳቢ ባልነበሩት ቀሪ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በኢትዮጵያ ቡና በኩል እያሱ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጭ ከወጣችበት እንዲሁም በመቐለዎች በኩል ደግሞ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አማኑኤል ገ/ሚካኤል ወደ መሀል ያሻማውንና ኦሲ ማውሊ ለጥቂት ሳይደርስባት የቀረችው ኳስ በስተቀር በጭቃማው ሜዳ ላይ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ለመመልከት ሳንችል ቀርተናል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ እንዲሁ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመጠኑም ቢሆን የተሻለ እንቅስቃሴዎች ነበሩ ፤ በ47ኛው ደቂቃ መቐለዎች ያገኙትን የተሻለ የማግባት አጋጣሚ ኦሲ ማውሊ ከወንድወሠን ጋር ተገናኝቶ ያመከናት እንዲሁም በ52ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ከመቀሌዎች የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ሶስት ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ የሞከራትና ኦቮኖ በአስደናቂ ሁኔታ ያዳናት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

መቐለዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስ በሚያጡበት አጋጣሚ በተሻለ ቅርጻቸውን ጠብቀው በመከላከል አልፎ አልፎ በተሻጋሪ ኳሶች አደገኞች ነበሩ፡፡ በጨዋታው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች እንግዳዎቹ ከጨዋታው የተሻለ ነገር ይዘው ለመውጣት የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት አሳይተው ነበር። በተለይም በኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር በኩል የመስመር ተከላካዮ ወደፊት በተጠጋባቸው አጋጣሚዎች በረጃጅም በሚላኩ ኳሶች በአማኑኤል አስደናቂ የአግድሞሽ ሩጫ በመታገዝ ኢትዮጵያ ቡናን በተደጋጋሚ መፈተን ችለዋል። ለአብነትም በ78ኛና በ79ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ መሀል ያሻገራቸውን ኳሶች ወንደሠን አሸናፊ ግብ ከመሆን አገዳቸው እንጂ እጅግ አደገኛ ነበሩ፡፡

በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ያሬድ ብርሃኑ የጨዋታውን ውጤት ልትቀይር የምትችል ወሳኝ አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፤ በዚህም ጨዋታው 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡