ወልቂጤ ከተማ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል

የከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ቻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ወልቂጤ ከተማ ደግአረግ ይግዛውን ለመቅጠር ከስምምነት መድረሱን አስታውቋል። 

አሰልጣኝ ደግአረግ ከዚህ ቀደም በባህር ዳር ከተማ በ2001 ከዛም በባህርዳር ዩንቨርስቲ እና አውስኮድ ከሰሩ በኋላ ከ2009 ጀምሮ በኢኮስኮ ሲሰሩ ቆይተው ወደ አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ቡድን ማምራታቸው ተረጋግጧል። ” ማረፊያዬን ወልቂጤ ከተማ አድርጌያለሁ። ለምመርጠው አጨዋወት የሚመቹ ነገሮችን ያሟላ ክለብ መሆኑን ተገንዝቤ ቀጣዩን ዓመት አብሬ ለመስራት ወስኛለው። በዚህም ደስታ ይሰማኛል። በቆይታዬም ከአመራሩ ጋር በመተባበር የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ጥረት አደርጋለው። ለኔም ለክለቡም መልካም የስራ ጊዜን እመኛለሁ። የተለያዩ ጥያቄዎች ቢደርሱኝም ከክለቡ ጋር ለመስራት መወሰኔን በዚሁ አጋጣሚ ማሳወቅ እፈልጋለሁ። ” ሲሉ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአሰልጣኝ ቅጥሩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ደግሞ ይህን ብለዋል። ” ዘንድሮ እንደማደጋችን ሳይሆን እኛ ኳሱ ውስጥ ብዙ የምናስተውላቸው ነገሮች አሉ። ከዛ ውስጥ አንደኛው ነገር አሰልጣኝ ቅጥር ነው። ማንኛውም ቡድን ሲቋቋም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ግብአት ያለው ተጫዎቾች ማፍራት አላማው ነው። እስካሁን ባለው አካሄድ ይህ ነው የሚባል ልዩነት ማየት ያልቻልነው በአሰልጣኞች ቅጥር ምክንያት ነው። ከዚህ ቀደም ያሉት በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ የፕሪምየር ሊግ ቡድን ይዘው ላለመውረድ ሲጠጋ ጥለው የሚወጡ ናቸው። አሁን ላይ የቀጠርነው አሰልጣኝ በትምህርት ደረጃውም ሆነ በካፍ ላይሰንስ ብቁ ነው። በወጣቶች ላይ የሚያምን፣ በሰራቸው ቡድኖች ላይ ማራኪ የኳስ ፍሰት የሚያሳይ እና ጠንካራ ቡድን የሚሰራ ነው። ወልቂጤ ከተማ በዘንድሮ ውድድር ዓመት ብዙ አዳዲስ ነገር ይዞ ብቅ ይላል ዛሬ የሰማችሁት አዲስ አሰልጣኝ ይዞ መምጣቱን ነው። በቀጣይ ብዙ ነገር ጠብቁ። በአጠቃላይ በአዲሱ የአሰልጣኝ ቅጥር እጅጉን ደስተኛ ነን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡