አዳማ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ተስማማ

የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ቅጥር በመፈፀም ክረምቱን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት እና የግራ መስመር ተከላካዩ አስናቀ ሞገስን ወደ ቡድናቸው ለመቀላቀል ተስማምተዋል።

ባለፈው ዓመት ደደቢትን ለቆ ወደ ወላይታ ድቻ በማምራት የቡድኑ ቀዳሚ ተመራጭ የነበረው ቁመተ መለሎው ግብ ጠባቂ ታሪኬ ጌትነት አዳማ ከተማን ለመቀላቀል የተስማማ የመጀመርያው ተጫዋች ሲሆን ወደ ሆሮያ ያመራው ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራ ቦታ የሚተካ ሲሆን ለቋሚ ተሰላፊነት ከ ዲሪ. ኮንጓዊ ጃኮ ፔንዜ ጋር ይፎካከራል።

ሌላው ወደ አዳማ ከተማ ለመቀላቀል የተስማማው የግራ መስመር ተከላካዩ አስናቀ ሞገስ ነው። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ መጫወት የቻለው አስናቀ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በተለይ የመጀመርያ ዙር ላይ ጠንካራ የነበረው እና ጥቂት ግቦች ያስተናገደው የባህር ዳር ከተማ ተከላካይ ክፍል ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ነበር የውድድር ዓመቱ ያገባደደው። በአዳማም ለተሰላፊነት ከአንጋፋው ሱሌይማን መሐመድ እና ወጣቱ ብሩክ ቦጋለ ጋር የሚፎካከር ይሆናል።

ቀድመው አሸናፊ በቀለ አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት አዳማ ከተማዎች ሁለቱን ተጫዋቾች ከሦስት ቀናት በኋላ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት በይፋ እንደሚያስፈርሙ፤ ተጨማሪ ተጫዋቾችንም ወደ ቡድኑ እንደሚቀላቅሉ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡