የአሰልጣኞች ገፅ፡ ቆይታ ከፋሲል ተካልኝ እና ዕድሉ ደረጄ ጋር (ክፍል ሁለት)

ፋሲል ተካልኝ እና ዕድሉ ደረጄ በቅርቡ በውጭ ሀገር ተከታትለውት ስለመጡት ትምህርት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በቪድዮ ዩቲዩብ ቻነላችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ይህንን ቆይታ በፅሁፍ ማግኘት ለምትፈልጉ በሚከተለው መልኩ አዘጋጅተነዋል፡፡  ክፍል 1 (LINK)


ቃለ-ምልልሱን በቪድዮ ለመመልከት፡ YOUTUBE


ከሰለጠነው የእግርኳስ ዓለም የቀሰማችሁትን እውቀትና የገበያችሁትን ትምህርት በአግባቡ ወደ ተጫዋቾች ለማድረስ ወይም ለሌሎች አሰልጣኞች ለማጋራት ሥጋት የሚሆኑባችሁ ተግዳሮቶች ምንድን ይሆናሉ?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ስለ ሃገራችን እግርኳስ ብዙ ተነጋግረናል፤ በውስጡ ያሉት ችግሮች እንዳሉ ናቸው፤ ይሄ ግልጽና የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ባሉት ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነንም ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ሜዳ ላይ ለማሰለጥናቸው ተጫዋቾች ከውጪው ትምህርት ያገኘኋቸውን ጥሩ ነገሮችን ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ ብዙ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ደካማውን ጎን ብቻ እያነሳን እስካሁን ድረስ መፍትሄ ማበጀት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ እኔ መልካሙን ለማሰብ እሞክራለሁ፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ቆይታዬ ያገኘኋትን ልምድ ለጓደኞቼ ማካፈል እችላለሁ፤ የማውቀውን ነገር ለተጫዋቾቼ በቀላሉ  እንደማስተላልፍ አምናለሁ፤ በዚህ መልኩ ነው የማስበው፡፡

+ በቅርቡ ከአንጋፋው አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ ጋር ባደረግነው ውይይት ” በእኛ የአሰልጣኝነት ዘመን አሰልጣኞች ባህር ማዶ ተምረው ሲመለሱ አልያም ከውጪ ሃገር ባለሙያዎች ወደ ሃገራችን ሲመጡ በተጫዋቾች ዘንድ የሚታየው የቋንቋ ችግርና በቂ ያልሆነ የትምህርት ዝግጅት አዲስና ዘመነኛ እግርኳሳዊ ትምህርቶችን በቀላሉ ለማስረጽ አዳጋች ሁኔታን ይፈጥር ነበር፡፡” ብለዋል፡፡ ያኔ የሚስተዋሉት እነኚህ መሰረታዊ ችግሮች አሁንም ይኖሩ ይሆን?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ እኔም ከዚያው ማህበረሰብ የወጣሁ ነኝ፡፡ የተነሱት ችግሮች “አልነበሩም!” ማለት አይቻልም፡፡ አሁንም ይኖራሉ፤ ነገርግን ‘ችግሮቹን የመቋቋም ኃላፊነት የእኔ ነው፡፡’ ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢንስትራክተር ካሳሁን አሰልጥኖኛል፤ ሲያሰለጥነኝ ተቸግሮ ነበር ማለት ነው፡፡ እርሱ የገጠመው ችግር እኔንም ሊገጥመኝ እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ መልካሙ ነገር ላይ ብናተኩር ጥሩ ነው፡፡ አንዳንዴ <Academically> በጣም ጥሩ የሆኑ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ነገሮችን የመረዳት አቅማቸው ደካማ ሆኖ አግኝቻለሁ፡፡ በትምህርቱ ጥሩ ሳይሆኑ ለእግርኳስ የተፈጠሩ ደግሞ አሉ፤ ገና ስትናገር ቀድመውህ ማሰብ የሚጀምሩ ምርጥ ተጫዋቾችን አይቻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ መደምደም የሚቻል አይመስለኝም፤ እኔም መደምደሙን አልፈልገውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የእግርኳሳችንን ችግሮች ብቻ ስንናገርና መሰናክሎችን ስንዘረዝር እዚህ ደርሰናል፤ እስካሁን ግን ችግሮቹ አልተፈቱም፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች እኔ ስጫወትም የነበሩ ናቸው፤ ዛሬም ግን እንደ አዲስ ይነሳሉ፡፡ የሚያሳስበኝ ‘እነዚያን ችግሮች የሚቀርፈው ማን ነው?’ የሚለው ነው፡፡ ሲስተሙ ራሱ እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ እድሉ ውጪ ተምሯል-ወጣቶች ላይ፡፡ እስቲ ምን ያህል ክለቦቻችን ናቸው የተደራጀ የወጣቶች አካዳሚ ያላቸው? መመለስ አይቻልም፤ አስቸጋሪ ነው፡፡

★ ዕድሉ ደረጀ፦ ከፋሲሊቲ አንጻር ብቻ እንኳ ብዙ ነገሮች እንደሚቀሩን በጣም ግልጽ ነው፡፡ እጅግ ወሳኝ ከሆነው ብጀምር ከፍተኛ የሆነ የሜዳ እጥረት አለ፡፡ አብዛኞቹ ክለቦች የራሳቸው ሜዳ እኮ የላቸውም፤ በእርግጥ በፕሪሚየር ሊግ በአንዳንድ ክልሎች ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው፡፡ ይሁን ይሰሩ – ለፕሪሚየር ሊግ ብቻ ካልሆኑና ወጣቶችን ለማፍሪያነት ከዋሉ ጠቀሜታቸው አያጠያይቅም፡፡ በስፔን ቆይታዬ ክፍል ውስጥ ትምህርታችንን በምንከታተል ጊዜ በየሃገሮቻችን ከየትኛው የእድሜ ደረጃ ስልጠና እንደምንጀምር ልምዶቻችንን ማሰማት ሲኖርብንና ከበርካታ ሃገራት የመጡ ሰልጣኞች ተመክሮዎቻቸውን አካፍለው ተራው እኔ ጋር ሲደርስ ‘ይለፈኝ!’ የምልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ እኛ ጋር በፌዴሬሽኑ ሥር ክለቦች የሚያካሂዱት ውድድር ከ17 ዓመት በታች ነው፡፡ በእርግጥ አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብዙ ባያስቆጥርም ከ15 ዓመት በታች ውድድር ያካሂዳል፤ ዘንድሮ ደግሞ ከ13 ዓመት በታች ውድድሮችን ማዘጋጀት ጀምሯል፡፡ በእነዚህ የእድሜ እርከኖች ስለሚሰሩ የእግርኳስ ቡድኖች ለክለብ ኃላፊዎች ለማስረዳት ራሱ ብዙ ማማጥ ይጠይቃል፤ በሚገባቸው ቋንቋና በሚረዱት ገለጻ ማስረዳት የግድ ይላል፡፡ እውቀቱና ልምዱ ያላቸው የክለብ አስተዳዳሪዎች የሉም ማለቴ አይደለም፤ ስለ እግርኳስ ሳያውቁ ቦታውን ለያዙ ሰዎች ግን ማሳመን ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ወደ ታች ወርደህ ስትሰራ ጠንካራ መሰረት የመጣል እድል ቢኖርም ተጫዋቾቹን ወደ ላይ ለማሳደግ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ወዲያው ወዲያው የበሰለ ነገር ለሚፈልጉ ክለቦች ደግሞ ከታች የማሳደጉ ሒደት ሊርቅባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ በታችኛው የእድሜ እርከኖች ውድድሮችን የማግኘት ከፍተኛ ችግር ይገጥማል ማለት ነው፡፡ በስፔን ፌዴሬሽኖች ከሚያዘጋጁት ሌላ የግል ሊጎችን የሚያሰናዱ ማሕበራት (Associations) አሉ፡፡ ከስድስት ዓመት የእድሜ እርከን ጀምሮ ማንኛውም ቡድን በፈለገው ሊግ (የግል-ከ- ፌዴሬሽን) የመወዳደር አማራጭ አለው፡፡ የማምነው ይሄም መጀመር እንዳለበት ነው፡፡ ፍላጎቱ፣ ጥረቱ እና አቅሙ ያላቸውን ሰዎች በማብዛት የእያንዳንዱን አካል ትንሽ አስተዋጽኦ አሰባስቦ ነገ ትልቅ ውጤት ማሳካት ይቻላል፡፡ ዋናው ‘መንገዶች ድፍንፍን ያሉ ናቸው፡፡’ ብሎ እጅን አጣጥፎ አለመቀመጥ ይመስለኛል፤ በቃ ባለው ነገርም ጀምሮ ማሳየት ነው፡፡ እኔም በትንሹ እንደ <Pilot Projects> አይነት ትንሽ ሥራ ለመጀመር አስቤያለሁ፡፡ ‘ይዤ የመጣሁት መጠነኛ ልምድ የሆነ ቦታ ላይ ማረፍ ይኖርበታል፡፡’ ብዬ ስለማምን በምችለው አቅም አስፍቼ ለመስራት፣ ከተሳካም ሃገር ላይ ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

“በሃገራችን እግርኳስ በርካታ የቴክኒክ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም ስልጠናው ወደኋላ አስቀርቷቸዋል፡፡” ተብሎ በስፋት ይነገራል፡፡ እውነት የሚባለውን ያህል ቴክኒካዊ ተሰጥኦ አለን?  የቴክኒክ አተረጓጎማችን አልያም አረዳዳችን ትክክል አይደለ ይሆን? ስልጠናችንስ በተፈጥሮ የሚገኝ የቴክኒክ ችሎታን ማዳበር ይችላል?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ለመሆኑ ‘ በጣም ብዛት ያላቸው ቴክኒካል ተጫዋቾች አሉን፡፡’ ሲንል ከእነማን ጋር አነጻጽረን ነው? እግርኳስ’ኮ ሜዳ ላይ የሚታይ ነገር ነው፡፡ በተጻራሪው ‘ምንም አይነት የቴክኒክ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች የሉንም፡፡’ የሚል ጨለምተኛ አስተሳሰብም የለኝም፡፡ በየሰፈሩ ኳስ በጣም ጎበዝ የሆኑ ልጆች አሉ፤ ቁምነገሩ ‘እነዚህን ልጆች እንዴት እናሳድጋቸው?’ የሚለው ነው፡፡ ላይ (በብሔራዊ ቡድንና ክለብ ደረጃ) ሲደርሱ ቴክኒካዊ ችሎታቸው እየቀነሰ የሚሄደው ለምንድነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ብንወያይ እና በርካታ ቴክኒካል ተጫዋቾችን ብናፈራ ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ‘ተጫዋቾቻችን ቴክኒክ አላቸው፤ የላቸውም፡፡’ ብሎ መሟገት ለእኔ ተራ ክርክር ነው፡፡ ምክንያቱም ‘ተጫዋቾቻችን በቴክኒክ በጣም ጎበዝ ናቸው፡፡’ የምንለውን በተግባር ማረጋገጥ መቻል ይኖርብናል፤ በትክክል ማሳየትም ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ ‘የብራዚል ተጫዋቾች በቴክኒክ ችሎታቸው የላቁ ናቸው፡፡’ የሚለውን አባባል ለዓለም አሳይተዋል፡፡ አፋችንን ሞልተን ለመናገር መጀመሪያ የተጫዋቾቻችንን የቴክኒክ አቅም ማረጋገጥ አለብን፡፡ ከዚያ ውጪ ‘በየሰፈሩ የምናያቸው ታዳጊዎች የያዙትን የቴክኒክ አቅም እንዴት ባለ መልኩ እንጠቀምበት?’ የሚለው ሃሳብ ላይ ማተኮር የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ታዳጊዎች ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትን ስልጠና ከታችኛው የእድሜ እርከን የማስጀመር መንገዶችን ማመቻቸት አለብን፡፡ ለዚህ ሃገር እግርኳስ ሲሉ ያለምንም ጥቅም በየሰፈሩ ህጻናትን የሚያሰለጥኑ ወጣቶች አሉ፡፡ ጃንሜዳ ብትሄድ ትገረማለህ! እድሉ እንደጠቀሰው እነዚህን አሰልጣኞች ማስተማር ወሳኝ ነው፡፡ አሰልጣኞቹ ለታዳጊዎቹ የእድሜ እርከናቸውን መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎችን እንዲሰጡ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ በየመንገዱ የሚጫወቱ ታዳጊዎችን ችሎታ በሃገር ደረጃ መጠቀም እንችላለን፡፡ ወደ ክርክሩ ከሄድን ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ ከሌሎች ሃገራት የተሻለ የቴክኒክ ችሎታ እንዳለን የትነው ያረጋገጥነው? መልስ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እኔም’ኮ መንገድ ዳር ስጫወት አድጌ ነው ኳስ ተጫዋች የሆንኩት፤ አሰልጣኝ አግኝቼ አቅጣጫ ልይዝ የተሞከረው ምናልባት አስራ ስምንት አልያም አስራ ዘጠኝ ዓመቴ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ ቴክኒኩን የተማርኩትም ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ ሃሳቡ አከራካሪ ነው፡፡ ስለዚህ ክርክሩን ትተን መስራቱ ነው የሚያዋጣን፡፡

★ ዕድሉ ደረጀ፦ ብዙውን ጊዜ <Issue> ያልሆኑ ነገሮች (ክብደት ሊሰጣቸው የማይገቡ ጉዳዮች) <Issue> ሲሆኑ (ትልቅ ትኩረት ሲያገኙ) ይታያል፡፡ የትኛውም ዓለም ላይ የሚገኝ ተጫዋች ቴክኒክን በተገቢው ደረጃ ካገኘ ማግኘት ይችላል፤ በቃ! ምንም እኮ የሚያከራክር አይደለም፡፡ አንድ ተጫዋች በሚፈለገው የእድሜ እርከን ቴክኒክን ከተማረ የተሰጠውን ቴክኒካዊ ትምህርት ይይዛል፡፡ ፈረንጆቹ ከአካዳሚ ውጪ ታዳጊ ተጫዋቾች የሚያገኟቸውን ልምምዶችና የሚማሯቸውን ቴክኒኮች <Invincible> ይሉታል፡፡ ለምሳሌ ዮሃን ክሯይፍ “በሳምንት ለሶስት ቀናት ወደ አካዳሚ ሄጄ እማራለሁ፤ በቀን ሁለቴ ደግሞ ሰፈሬ በሚገኙ ሜዳዎች ልምምድ አደርጋለሁ፡፡ ታዲያ ለእኔ ትምህርት ቤት የቱ ነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡ የአካዳሚው የተደራጀ ሥልጠና (Structured Training) እና የሰፈሩ ልምምድ (Invincible Training) ክሯይፍን ሙሉ ተጫዋች አድርጎታል፡፡ ስለዚህ መሰረቱ ያለው ሥራው ላይ ነው ማለት ነው፡፡ “ቴክኒካዊ ችሎታ አለው፤ የለውም፡፡” አይደለም ቁምነገሩ፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔና ፋሲል በመጣንበት መንገድ እና ባገኘነው ሥልጠና የፈለገውን ያህል ብንጥር <Professional> መሆን አንችልም ነበር፡፡ ነገርግን በእድሜ ደረጃችን በቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ አካል ብቃትና ሥነ ልቦና የሚገባንን ሥልጠና አግኝተን ቢሆን ኖሮ <Professional> ደረጃ የመድረስ እድላችን ይሰፋ ነበር፡፡ አንድ ማመሳከሪያ ልስጥ፥ በጆአኪም ፌኸርት አማካኝነት ቢንያም በላይ በጀርመን ክለቦች ለመጫወት ይችል እንደሆነ የተሰራለትን የብቃት ግምገማ (Assessment) አይቼው ነበር፡፡  ከሙከራው የተገኘው ውጤት የሚያሳየው ቢንያም አሁን ባለው ብቃት መጫወት የሚችለው በጀርመን የሁለተኛው ሊግ እርከን ላይ ነው፡፡ አንድ ተጫዋች በቡንደስሊጋ-2 ለመጫወት እንዲችል ደግሞ ዜግነቱ ጀርመናዊ አልያም የ<UEFA> አባል ሃገር መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ቢንያም በዚህ ምክንያት ወደ አልባኒያ ሄደ፡፡ እኛም ያደግንበት፣ የአሁኖቹም ተጫዋቾች እያገኙት ያለው የቴክኒክ ሥልጠናም ሊያጫውተን የሚያስችለን ደረጃ ይህን ያህል ነው፡፡ ምናልባት በትልልቅ ሊጎች ውስጥ የሃገራችንን ተጫዋቾች የማናገኝበት ምክንያትም ይህ ይመስለኛል፡፡ እስከ ስድስት ዓመት የእድሜ ክልል ለሚገኙ ተጫዋቾች የ<Basic Motor Skill> እና <Specific Motor Skill> ልምምዶች በአግባቡ ሲሰጣቸው አስራ ሰባት ዓመታቸው ላይ ሲደርሱ ምን አይነት ብቃት እንደሚኖራቸው ማሰብ ነው፡፡ ልዩነቱ ሥራ ነው፡፡ ሙግቱን ትተን መሰረታዊ ሥራዎች ላይ እናተኩር፡፡ በአለምአቀፍ ደረጃ የሚሰራው <World Class Coaching> ድረገጽ ላይ አንድ መጽሃፍ ሳነብ <Progressive Training Method> የሚሰኝ አርዕስት ሥር ስለ ሊዮኔል ሜሲ የኳስ ቁጥጥር (Ball Control) ችሎታ ሲተነትን ክህሎቱ ተፈጥሮዓዊ ተሰጥኦ (Innate) እንዳልሆነ ያብራራል፡፡ ይልቁንም በማይታክትና በማያቋርጥ ልምምድ ያዳበረው ስለመሆኑ ይዘረዝራል፡፡ አንዴ ከጆአኪም ፌኸርት ጋር አንድ ጀርመናዊ ባለሙያ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ሥልጠና ለመሥጠት እዚህ መጥቶ በአስተርጓሚነት ሄጄ ነበር፡፡ ከፌኸርት ጋር የመጣው ባለሙያ አሰልጣኝ ነው፡፡ በሥልጠናው ወቅት ” ተመሳሳይ የቴክኒክ ችሎታ ያላቸው ሁለት ተጫዋቾች ቢኖሩ፥ አንደኛው ለሁለት ዓመት ተገቢ ልምምድ ቢያደርግ፣ ሌላኛው ደግሞ ምንም ሳይሰራ ቢቆይ ከሁለት ዓመታት በኋላ ካልሰራው ተጫዋች አንጻር ሥልጠናውን በአግባቡ የተከታተለው ተጫዋች የቴክኒክ ብቃቱ ይበልጥ አድጎና ጎልብቶ ይገኛል፡፡” ይል ነበር፡፡ ” ተጫዋቹ ምንም እንኳ ተፈጥሮ የለገሰችው ተሰጥኦ ቢኖረውም ያን ለማሳደግ ካልጣረ ጭራሹኑ የነበረውን እያጣ ይሄዳል፡፡” በማለት ያስረዳ ነበር፡፡ ስለዚህ ወሳኙ ነገር ሥራ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችም በሚፈለገው እድሜ አስፈላጊውን ሥልጠና ካገኙ እድሎች አሉ፡፡ ለሰው ልጅ የተሰጠው እድል፥ ለስፔናዊው፣ ኡጋንዳዊው፣ ናይጄሪያዊው፣… የተቸረው እድል እኛም ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጠንክረን ከሰራን እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ ይህንን አብቅተን ለማምጣት መጣር ነው የሚጠበቅብን፡፡ ሙግቱንና ክርክሩ ላይ ጊዜያችንን ከምናጠፋ ስራ ላይ ብናተኩር የተሻለ ነው፡፡ አለበለዚያ ትርፉ ጉንጭ ማልፋት ነው የሚሆንብን፡፡

ለአሰልጣኞች ምቹ ከባቢያዊ ድባብ ለመፍጠር የክለብ አመራሮችና እግርኳሱን የሚያስተዳድሩ አካላት ድርሻ ምን ይሁን? እንደው እነርሱም የ<Football Management> ትምህርት ይማሩ እንዴ?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ችግሩ ለቦታው ተገቢው ሰው ከተገኘ ይቀረፋል፡፡ እግርኳሱን እየመራ ያለ አንድ ሰው ከአሰልጣኙ የሚፈልገውን ለመጠየቅ አልያም አሰልጣኙን ተጠያቂ ለማድረግ በእግርኳስ ቋንቋ መግባባት መቻል አለባት፡፡ አሰልጣኙን ለመገምገም ከፈለገ እንኳ እርሱ ራሱ በቅድሚያ ስለ እግርኳስ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ካለበለዚያ ግንኙነቱ ዝምብሎ ተራ ክርክር ነው የሚሆነው፡፡ ለዚ’ኮ ነው ሁልጊዜ አለመግባባት የሚፈጠረው፡፡ በአስተዳደሩ በኩል የተቀመጠ የመመዘኛ ሥርዓት ካለ አሰልጣኙ በዚያ መንገድ ሊገመገም ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህን ‘ሲስተም’ ለመንደፍ በመጀመሪያ ክለቡን ወይም ቡድኑን የሚመራው አካል እግርኳሱን ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል፤ ከተቻለም በዚሁ ዘርፍ የተማረ መሆን አለበት፡፡  ይህ ብዙ ዓመት የተወራበት ጉዳይ ነው፡፡ “ስፖርት፥ ስፖርቱን በሚያውቅ ሰው ይመራ!” በተደጋጋሚ ረዘም ላሉ ጊዜያት ተወራ፤ ተወራ፤ … ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ለውጥ አልታየም፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ክለብ ውስጥ ለቡድን መሪነት የሚመረጠው ማን ነው? ምናልባት ከአስተዳደር ቢሮ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ያ ቡድን መሪና አሰልጣኙ እንዴት ነው ሊግባቡ የሚችሉት? ሁለቱ ባለሙያዎች ስለ እግርኳስ የሚኖራቸው የእውቀት ደረጃ የተለያየ ነው፡፡ በምን መልኩ ሊረዳዱ ይችላሉ? እግርኳሱ ውስጥ ቴክኒክ፣ ታክቲክ፣ የአካል ብቃትና ስነ ልቦና ሁሌም በመሰረታዊነት የሚነሱ ነጥቦች ናቸው፡፡ ከባቢያዊ ሁኔታዎችም የነዚህኑ ያህል ወሳኝ ናቸው፡፡ አንድ አሰልጣኝ በትኩረት ሥራውን እንዲሰራ በዙሪያው የሚገኙ ድባቦች አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ፡፡ አሰልጣኙ የተፈለገውን ያህል የተማረ ቢሆን፣ በሥልጠናው ዘርፍ ብልህና ምጡቅ አዕምሮ ቢይዝ፥ ለሥራው የተመቻቸ አካባቢ ውስጥ ካልተገኘ ያካበተውን ልምድና እውቀት በቀላሉ ወደ ቡድኑ ለማሸጋገር ይቸገራል፡፡ አውሮፓ ውስጥ ክለቦች አሰልጣኝና ቴክኒክ ዳይሬክተር አላቸው፡፡ የቴክኒክ ዳይሬክተሩን የኋላ ታሪክ ብንቃኘው በእግርኳስ ውስጥ ያለፈ ወይም ስለ እግርኳስ የተማረ፣ የእግርኳስ ቋንቋን መናገር የሚችል፣ በማንኛውም እግርኳሳዊ ጉዳይ አሰልጣኙን መጠየቅ የሚያስችል አቅም ያለው ሰው ነው፡፡ እኛ ሃገር ግን እንደዚህ ዓይነት ኃላፊነት የሚወጡ ባለሙያዎችን ማግኘት አይቻልም፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ትክክለኛውን ሰው ተገቢ ቦታ ላይ በማስቀመጥ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ አንድን የህክምና ዶክተር በማምጣት አሰልጣኝ ማድረግ አይቻልም፤ የእግርኳስ አሰልጣኙንም ወስደህ በህክምና ሙያ ላይ ማሰማራት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ግን እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ የእግርኳስ ቡድንን የሚያስተዳድሩ ባለሙያዎች ስለ እግርኳሱ ብዙም እውቀት የሌላቸው ስለሆኑ ዘወትር ግጭቶችና ንትርኮች ይፈጠራሉ፤ እነዚህ አለመስማማቶች ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ የእግርኳስ አስተዳደራዊ መዋቅራችን በጣም ደካማ ነው፡፡ በትክክለኛው መንገድ የሚያሰራ ሲስተም አልተዘረጋም፤ በዚህ ሁኔታ ይህን ችግር መቅረፍ በጣም ከባድ ይሆናል፡፡ አንድ የክለብ አመራር ” ከዚህ ተነስቼ ይህኛው ደረጃ ላይ መድረስ አለብኝ፡፡” የሚል እቅድ አስቀምጦ ተፈጻሚ ሳያደርግ ሲቀር በግምገማ ‘ስህተታችን የቱ ጋር ነው?’ በማለት ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩርና አቅም የማሳደግ ሥራ የሚሰራ ኃላፊ ያስፈልጋል፤ ያኔ አሰልጣኙም ተጠያቂ ይደረጋል፡፡

+ ሁሌም ” እግርኳስ ስፖርቱን በሚያውቅ ሰው ይመራ!” የሚል ሃሳባዊ መፍትሄ ይሰጣል፡፡ የእግርኳሱን አስተዳደራዊ ቦታ በጥሩ ብቃት የሚመሩ በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ በርካታ ሰዎች አሉን ብላችሁ ታስባላችሁ?

★ ዕድሉ ደረጀ፦ እዚህ ላይ ነባራዊውን ሁኔታ ሳይሆን ‘ይህን ብቁ ባለሙያ ለማፍራት ምን ያህል ርቀት ሄደናል?’ የሚለው ጉዳይ በጣም መጤን አለበት፡፡ ‘ ታስቦበት (Deliberatetely) ይህን መሰል ብቁ መሪ ወደ እግርኳሱ ለማምጣት አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረው ተሰርቶባቸዋል ወይ?’ ብለህ ስትጠይቅ ‘የሉም! አልተፈጠሩም!’ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እኛም የመጣነው በግል ጥረት ነው፡፡ ጉዳዩን ወደ አንድ ጥግ አንውሰደው፤ ይህ መታሰብ ያለበት ነገር ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰው ከምንም ቦታ መጥቶ የእግርኳሱ አስተዳደር ላይ የተሻለ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡ ተምረውም ሆነ በልምድ እግርኳሱን በደንብ ሊያግዙና ሊረዱ የሚችሉ ሰዎች በዓለም ላይ ታይተዋል፡፡ “አማራጩ ይህ ብቻ ነው” ማለት ሳይሆን “ስፖርታዊ ልምዱ ያለው ወደ ቦታው ቢመጣ የተሻለ ይሆናል፡፡” ከሚል እሳቤ አንጻር ቢታይ ጥሩ ነው፡፡ እግርኳሱን የሚመሩ ባለሙያዎች ስለማፍራት እቅድ ስናወጣም በእግርኳሱ ያለፉ ሰዎች እንዲበዙ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው፡፡ ለአንድ የእግርኳስ አሰልጣኝነት ቅጥር ማስታወቂያ ሲወጣ መስፈርቱ ላይ “በስፖርት ሳይንስ ዲፕሎማ ያለው!” ብለህ ስትጀምር ገና ነገሩ ሁሉ ያበቃለታል፡፡ አስራ ምናምን ዓመት ተጫውቶ ያሳለፈውን ባለ ብዙ ልምድ ሰው ትገድበዋለህ ማለት ነው፡፡ ወሳኙ ጥያቄ ‘እንደዚህ አይነቶቹን ሰዎች አሳታፊ የሚያደርጉ ከባቢዎች ተፈጥረዋል ወይ?’ የሚለው ነው፡፡ እነርሱን የሚያሰራ መዋቅር ሳይዘረጋ በስፖርቱ ያለፉ በቂና ብቁ የእግርኳስ ባለሙያዎች አልተፈጠሩም ማለት አይቻልም፡፡ ወረቀት እንኳ ባይኖር ልምድ ራሱ እኮ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሰሩ የሚችሉ የእግርኳስ ስራዎችን ለመስራት ያስችላል፡፡ ምንም ተግባራዊ ልምድ የሌለውን ሰው አምጥቶ ከማሰራት ይልቅ በልምድ ለሚሰራው ቅድሚያ ሰጥቶ ራሱን እያሻሻለ የሚሄድበትን መንገድ ማመቻቸት የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ጉዳዩን (Polarize አናድርገው) ጽንፍ አንስጠው፤ ሁኔታዎችን እናመቻች፡፡ የእግርኳስ አሰልጣኝነት ሙያ በትልቁ አየር እንደወሰደ ፊኛ ሊመሰል ይችላል፤ ፊኛው በትንሽ መርፌ ከጥቅም ውጪ እንደሚሆነው ሁሉ ለአሰልጣኞች ምቹ ነባራዊ ሁኔታዎች እስካልተፈጠሩ ድረስ ሁሌም ሥራቸው የአደጋ ጠርዝ ላይ ነው፡፡ ልክ እንደ መርፌዋ በአሰልጣኞች ቡድንህ ውስጥ ጥቂት ህጸጽ ከተፈጠረ ልፋትህ ከንቱ ይቀራል፡፡ ፋሲል ባለው ላይ የምጨምረውም ከአሰልጣኞች ጥሩውን ለማግኘት አጋዥ ከባቢያዊ ሁኔታዎች ይፈጠሩ ነው፡፡

ባልተመቻቹ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናችሁም ዘወትር ራሳችሁን ለማብቃት ትተጋላችሁ፡፡ ሌሎችም እንደ እናንተው የተሻሉ የትምህርት እድሎች እንዲያገኙ ምን ያድርጉ?

★ ፋሲል ተካልኝ፦ ሁሉም ነገር አጥብቆ ከመፈለግ ይጀምራል፡፡ እኔ ራሴን አንድ ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ወይም ህልሙን ለማሳካት እንደሚጥር አሰልጣኝ አድርጌ ነው የማየው፡፡ አቅሜን ሊያሳድግልኝ የሚችል አልያም የህልሜ ከፍታ ላይ ሊያወጣኝ መሰላል ይሆነኛል ብዬ የማስበውን ነገር ሁሉ እሞክራለሁ፡፡ እንዲያውም እድሉ አጠገቤ ስላለ ያስታውሰዋል፤ እኔና እርሱ አንድ ኮርስ በውጪ ሃገር ለመውሰድ የመሞከር አጋጣሚ ነበረን፡፡ ሁለታችንም ቪዛ የተከለከልነው አንድ ቀን ነበር፡፡ እድሉን አግኝተን፣ በግላችን ክፍያዎቹን ጨርሰን ቪዛ ግን ማግኘት አልቻልንም፡፡ በጊዜው ቪዛውን እንኳ ሊያሰጠን የሚረዳን አካል አጥተናል፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠው እንግሊዝ ሃገር ነበር፡፡ በእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር የተዘጋጀውን የ<B-Licence> ሄደን ለመማር ነበር ጥረታችን፤ ግን አልተሳካልንም፤ በቪዛው መከልከል ምክንያት፡፡ ተስፋ አልቆረጥንም፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ይመስለኛል እድሉ በግል ጥረቱ የስፔኑን ትምህርት እድል አገኘ፤ እኔም ኦሎምፒክ ኮሚቴው ያመቻቸልኝን አጋጣሚ ተጠቀምኩበት፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ከልብ መፈለግን ማስቀደም ነው፡፡ በመማር፣ በማንበብ፣ በሙያው ካሳለፉ ሰዎች ጋር በመወያየት፣ …ራስን መለወጥና ማሻሻል እንደሚቻል ካመንክ ሁሉንም አማራጮች ትፈልጋለህ፡፡ አሁን ለመማር ሁኔታዎች ቅርብ ናቸው፡፡ በእርግጥ በቦታው ተገኝቶ ልምዳቸውን መጋራት፣ የሚሰሩበትን መንገድ በአካል ተገኝቶ ማየት የተለየ ነገር ነው፡፡ ቤትህ ቁጭ ብለህም ደግሞ የራስን ጥረት ማድረግ ፍላጎት ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ የሆነ ግብ አስቀምጠህ እዚያ ግብህ ጋር ለመድረስ መውጪያ መንገድ ያስፈልግሃል፤ እነዚያ መንገዶችህ ጠንካራ ስራህ፣ ከስራህ የምታገኘው የየዕለት ተመክሮህ፣ መደበኛውና መደበኛ ያልሆነው ትምህርት፣…..ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን እግርኳስ ሁሉም ቦታ አለ፤ ለመማር ዝግጁ መሆን ነው፡፡ መደምደሚያዬ የሚሆነውም “ዋናው መፈለግ ነው፡፡ጥረት ማድረግ ነው፡፡ አጋጣሚው ቤት ድረስ እስኪመጣ መጠበቅ ሳይሆን አንተ ራስህ ወደ እድሎቹ መሄድ አብህ፡፡” የሚል ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አለምዓቀፉ የኦሎምፒክ ማህበር በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት እድሉን ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ፡፡

★ ዕድሉ ደረጀ፦ በራሴ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ነገር ቢኖር በግል ጥረቴ ያገኘሁትን የመማር እድል ሌሎችም እንዲያገኙ የሚመለከታቸውን አካላት ቀርቤ ለማናገር ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ሌሎችም እንደ’ኔው ካልተማሩ እኔ ብቻዬን ምንም ልፈይድ አልችልም፤ ፋሲልም እንዲሁ ብቻውን ምንም ሊፈጥር አይችልም፡፡ ስንበዛ ነው እኛ ራሳችን ተጠቃሚ የምንሆነው፡፡ አንድ <Drill> ለመፍጠር አራት-አምስት ብንሆን አንድ ብቻውን ሆኖ ከሚሞክረው በላቀ በዛ ያለ ተሳታፊ ሃሳብ የሰጠበት “ድሪል” ጥራት ያለው ሆኖ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው እና በዚህ ጉዳይ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ካልሰሩ እኔ እሰራዋለሁ ብዬ ያስቀመጥኩት ሁለተኛ እቅድ (Plan-B) አዘጋጅቻለሁ- በራሴ መንገድ፡፡ እኔ ሄጄ በመማሬ ብቻ በዚያ ትምህርት ቤት ለመማር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማሟላት ላይ የሚገኝ አካዳሚ ውስጥ ያለ ሰው አውቃለሁ፡፡ አየህ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሌሎችም ትምህርቱን መከታተል የሚፈልጉ ሰዎች አሉ ማለት ነው፡፡ በግሌ መጥተው ያናገሩኝ ሰዎችም አሉ፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለብኝ፡፡ ከዚያ ህብረት እንመሰርታለን፤ መስመሮችን እንፈጥራለን ማለት ነው፡፡ እኔ ትንሽ ነገር አግኝቻለሁ፤ በትምህርቱ ደረጃዬን አውቄያለሁ፥ ገና መሆኔን ተገንዝቤያለሁ፡፡ በጣም ትንሿን ነገር ይዣለሁ፤ ነገር ግን አሁንም ሰፊ እድሎች ይኖራሉ፡፡ በራሳችን ተደራጅተን እድሎቹን የምናመቻችበትን መንገዶች እፈጥራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ዋናው እኔንና ፋሲል መሰሎችን ማብዛት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ለውጥ እንፈጥራለን፡፡ እኛ የሚታይ ነገር ስንሰራ የሚመለከተንና ትናንት ጆሮ ያልሰጠን አካል ዛሬ ደግሞ ትኩረት ሊያደርግብን ይችላል፡፡ በራሴ ላደርግ የምችለውን ነገሮች በሙሉ እስከ ጥግ ድረስ ማስኬድና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች እድል እንዲያገኙ የተቻለኝን አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ የወጣቶቹ ፍላጎትና የእኛ ፈቃደኝነት ካለ እየበዛን እንሄዳለን፡፡

 በሰለጠነው የእግርኳስ ዓለም አንዳንድ አሰልጣኞች ተመክሮዎቻቸውን እና የተማሩትን ጋዜጦችና ድረገጾች ላይ አምደኛ በመሆን ለሌሎች ለማጋራት ይጥራሉ፡፡ ከዚያ አንፃር ያቀዳችሁት ነገር ካለ…

★ ፋሲል ተካልኝ፦ በሐሳብ ደረጃ እንግዲህ ባገኘሁት ልምድ ዙሪያ እንድጽፍና ተመክሮዬን እንዳካፍል የጠየቀኝ ድረገጽ አለ፡፡ እግርኳሱን የሚረዳ ከሆነ ይህን ማድረጉ አዳጋች ነው ብዬ አላስብም፡፡ ዋናው ነገር ለሃገራችን እግርኳስ ስሜት ያስፈልጋል፡፡ በእግርኳሱ ታዋቂና ተጠቃሚ ሆኖ መኖር ብቻ ሳይሆን እግርኳሳችን ሲቸገር አብረን የምንቸገርና ሊጎዳው ከሚመጣ ነገር ልንታደገው ዝግጁ መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግም ቅድሚያውን መውሰድ ያለብን እኛ ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ የማውቀውን ለሰዎች ለማካፈል፥ የማላውቀውን ደግሞ ከሰዎች ለመማር ምንም ችግር የለብኝም፡፡ እኔ እንድደርስ የማስበው ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብዬም አላስብም፤ ነገርግን ይብዛም ይነስም አሁን የምገኝበት ቦታ ላይ የደረስኩት ታላላቆቼ ባስተማሩኝ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ የማውቃት ትንሽ ነገር ካለኝ ለሌሎች ለማስተላለፍ ትልቅ ነገር ነው ብዬ አላስብም፡፡ ዋናው መልካም ነገሮችን ማሰብ ነው፡፡

★ ዕድሉ ደረጀ፦ እኔ ብዙ ልምድ አለኝ ብዬ አላስብም፡፡ እንዲያውም ፋሲሌ ለረጅም ዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እርከኖች ተጫውቷል፡፡ በአሰልጣኝነቱም በጣም የተሻለ ልምድ አለው፡፡ በርካታ ተመክሮዎቹን ያስተላልፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ አብርሐም ገ/ማርያም (የሶከር ኢትዮጵያ ድረገጽ ሥራ አስኪያጅ) ጋር ደውዬለት ተመክሮዎችን ከማጋራት ጋር በተያያዘ አውርተን ነበር፡፡ እውቀት የምንለዋወጥበትን መንገድ የመፍጠር የረጅም ጊዜ ፍላጎትም፣ ምኞትም ነበረኝ፡፡ የሆነ አካል መጥቶ እስኪያነሳሳህ መጠበቅ ሳይሆን አንተ ራስህ ነገሮችን መጀመር አለብህ፡፡ በግል ከማስተውላቸው ነገሮች መካከል Twitter ላይ በርካታ ተከታዮች ያሏቸው አካላት ተከታዮቻቸውን እንደ ትልቅ Investment ይመለከቷቸዋል፡፡ የተወሰነ እውቀት ይሰጧቸውና ሌላውን ደግሞ በገንዘባቸው እንዲያገኙ ያደርጓቸዋል፡፡ አየህ ባለሙያዎቹ ራሳቸው ያላቸውን እውቀት ይሸጣሉ፡፡ በእርግጥ እኛ እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም፤ ያለን እውቀትም ለመሸጥ የሚበቃ ላይሆንም ይችላል፡፡ ነገርግን እስቲ ይህንንም እንጀምረው፡፡ ከዚህ አንጻር ከአብርሃም ጋር ተወያይተን ይህን መድረክ እንዲያመቻች ተነጋገርን፡፡ አንድ እግርኳሳዊ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ ስትፈልግ ሌሎች ብዙ መጻሕፍትን ታገላብጣለህ፤ ያን ያነበብከውን ለሰዎች ለማካፈል ስትሞክር ደግሞ ራስህ ከአንዴም ሁለቴ ደግመህ የማንበብ አጋጣሚ ይፈጠርልሃል፤ ስለዚህ ውስጥ ይሰርጻል ማለት ነው፡፡ አንባቢዎችህ ደግሞ አንተ ያላየኸውን አቅጣጫ እየተመለከቱ ሌላ ተጨማሪ ግንዛቤ ይፈጥሩልሃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሰዎችን ጠቅመህ አንተም ተጠቃሚ የምትሆንበት ሁኔታ ይመቻቻል ማለት ነው፡፡ እኔም ያለኝን ሰጥቼ ከሌሎች ለመቀበል ከሚል አንጻር በቅርቡ አንዳንድ ጽሁፎችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡


ቃለ-ምልልሱን በቪድዮ ለመመልከት፡ YOUTUBE