ጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች ማስፈረሙን ቀጥሏል

በቅርቡ ወደ ዝውውሩ የገቡት በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው የሚመሩት ጅማ አባጅፋሮች የአራት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀቁ።

ኤልያስ አህመድ ከፈራሚዎቹ አንዱ ነው። ሰበታ ከተማን ለቆ ባለፈው ዓመት መጀመርያ ወደ ባህርዳር ያመራው ኤልያስ ለሊጉ እንግዳ በነበሩት ጣና ሞገዶቹ በቋሚነት በመጫወት መልካም እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን ጥሩ የተፈጥሮ ክህሎት እንዳለው ይነገርለታል።

ሌላው ቡድኑን የተቀላቀለው ሀብታሙ ንጉሴ ነው። የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ ተጫዋች ሀብታሙ በ2010 ለወልዲያ በመጫወት ያሳለፈ የአማካይ መስመር ተሰላፊ ነው።

ሦስተኛ ጅማ አባጅፋር የተቀላቀለው የተከላካይ ክፍል ተጫዋቹ ኤፍሬም ጌታቸው ነው። ወልዋሎዎች ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድጉ በርካታ ጨዋታዎች ላይ በአምበልነት የመራው ይህ ተጫዋች ባለፈው ዓመት ከበርካታ ዓመታት በኃላ ወደ ሰማያዊዎቹ ተመልሶም ቡድኑን በበርካታ ጨዋታዎች በአምበልነት መርቷል።

አብርሃም ታምራት የጅማ አራተኛው ፈራሚ ነው። ባለፈው ዓመት በደደቢት ያሳለፈው ይህ የአማካይ ተከላካይ ከዚ በፊት በወልቂጤ ከተማ እና በኢትዮጵያ መድን የተጫወተ ሲሆን በርካታ ተጫዋቾች ለለቀቁበት የጅማ አባጅፋር አማካይ ክፍል ጥሩ ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

አባጅፋሮች ለጊዜው ስሙን መግለፅ ያልፈለጉት እና በቅርቡ ይፋ ያደርጉታል ተብሎ የሚጠበቅ አንድ ወሳኝ ተጫዋች ማስፈረማቸውንም ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ