የሎዛ አበራ አዲሱ ክለብ ቢርኪርካራ ነጥብ ጥሏል

በ3ኛ ሳምንት የማልታ ቢኦቪ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ከሁለት ጨዋታ ሙሉ ስድስት ነጥብ የሰበሰቡትን ቢርኪርካራ እና ምጋር ዩናይትድን ያገናኘው እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁትን ቡድኖች ባገናኘው የማልታ ሴቶች ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ኪርፓፕ ዩናይትድን 7ለ1 ከረታው ስብስብ ውስጥ የአንድ ተጫዋቾች ቅያሬ አድርገው ወደ ዛሬው ጨዋታ የገቡት ቢርኪርካራዎች በኩል ሎዛ አበራ በተመሳሳይ ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከፊት በመሆን በመጀመርያ ተሰላፊነት ስትጀምር ጠንካራ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንግዳዎቹ ቢርቢካራዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ያገኟቸውን የግብ እድሎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

1ለ1 በተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሀሌይ ቡጊጃ በ28ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ ባለሜዳዎቹ መምራት ቢችሉም ተከላካይዋ አና ማሪ ሳኢድ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ ቢርቢካራዎች ለእረፍት በአቻ ውጤት እንዲለያዩ አስችላለች፡፡

በዛሬው ጨዋታ ላይ ሎዛ አበራ ግብ ማስቆጠር ባትችልም አሁንም በአራት ግብ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች። በተመሳሳይ ከክለቡ ጋር ላለፉት አራት ሳምንታት የሙከራ ጊዜ ስታሳልፍ የነበረችውና ዛሬ ረፋድ ላይ ለክለቡ በይፋ ፊርማዋን ያኖረችው እንግሊዛዊቷ የቀድሞ የፖርትስማውዝ ተጫዋች ኢስቴር አኑ ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን በተጠባባቂ ወንበር ላይ ማሳለፍ ችላለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ