ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀዋሳ ከተማ

ሀዲያ ሆሳዕና ከሦስት ዓመታት በኋላ የሚያደርገውን የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታውን በማሸነፍ ካለፈ ሳምንት ሽንፈቱ ለማገገም ወደ ሜዳ ሲገባ ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ድል አስመዝግቦ አጀማመሩን ለማሳመር ይፋለማል።

በክረምቱ በርካታ ተጫዋቾችን ያዘዋወሩትና በስብስብ ደረጃ ተፎካካሪ ቡድን ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚጠበቁት ሆሳዕናዎች ከቻምፒዮኑ መቐለ 70 ጋር ጠንካራ ፉክክር አድርገው በጠባብ ውጤት እንደመሸነፋቸው በዚህ ጨዋታ ቀላል ግምት አይሰጣቸውም።

ቡድኑ በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ጠጣር እና ከኳስ ውጭ በአምስት ተከላካዮች የሚጫወት ቡድን ይዞ የቀረበ ቢሆንም በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ የተለየ እና ማጥቃትን ያለመ አቀራረብ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ለኳስ ቁጥጥር አመቺ የሆኑ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾች የያዘ ቡድን መሆኑም ከረጃጅም ኳሶች በተቃራኒው ቅብብል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ይዞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የአማካዩ ሱራፌል ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ መሆን መልካም ዜና ሲሆን ፍራኦል መንግስቱ በጉዳት የነገው ጨዋታ ላይ የመኖር ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

የመክፈቻ ጨዋታውን ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ ጥሩ መነቃቃት ላይ ያለው ሀዋሳ ከተማ ከሜዳው ውጪ ጨዋታውን እንደማድረጉ አሰልጣኝ አዲሴ ካሣ ለጥንቃቄ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል። ከሜዳ ውጪ በአጨዋወትም ሆነ በተጫዋቾች ምርጫ ተገማች ያልሆነው ቡድኑ የፊት አጥቂው መስፍን ታፈሰ ፍጥነት እና ጉልበትን መሰረት ያደረገ የመልሶ ማጥቃት ይጠቀማል ተብሎ ሲገመት ቡድኑ በፈጣን የመስመር ሽግግር አደጋ የሚፈጥሩ ተጫዋቾችንም ይዟል።

በነገው ጨዋታ የውጪ ዜጎች እና በተክለ ሰውነት ጠንካራ በሆኑት የሆሳዕና የፊት መስመር እና ሀዋሳ የተከላካይ መስመር መካከል የሚኖረው ፍልሚያ ትኩረት የሚስብ ነው።

ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋን ሲገጥም በመጀመሪያው አጋማሽ ጉዳት የገጠመው መሳይ ጳውሎስን ጨምሮ አቤኔዘር ካሣ እና ጌትነት ቶማስ በጉዳት ወደ ሆሳዕና አላመሩም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሊጉ ከዚህ ቀደም 2 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ አንዱን ሲያሸንፍ በሌላኛው ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

– በሁለቱ ግንኙነታቸው በአስገራሚ ሁኔታ 11 ጎሎች ተቆጥረዋል። ሀዋሳ ከተማ ስድስቱን ሲያስቆጥር ሀዲያ ሆሳዕና አምስት አስቆጥሯል።

– ለመጨረሻ ጊዜ ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያደረጉት በአዳማ ከተማ ዋንጫ ፍፃሜ ሲሆን ሀዋሳ በብርሀኑ በቀለ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው።

– ሀዲያ ሆሳዕና ከ3 የውድድር ዘመን በኋላ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ የሜዳው ጨዋታ ያደርጋል። ለመጨረሻ ጊዜ በአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ጨዋታ ያደረገው ግንቦት 27/2008 ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና 2-1 ተሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

ታሪክ ጌትነት

ሱራፌል ዳንኤል – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ – ሄኖክ አርፌጮ

ይሁን እንደሻው – አብዱልሰመድ ዓሊ – አፈወርቅ ኃይሉ

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ – ኢዩኤል ሳሙኤል

ሀዋሳ ከተማ (4-1-4-1/4-2-3-1)

ቤሊንጌ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ኦሊቨር ኩዋሜ

አለልኝ አዘነ

ብሩክ በየነ – ሄኖክ ድልቢ – ዘላለም ኢሳይያስ – ብርሀኑ በቀለ

መስፍን ታፈሰ


© ሶከር ኢትዮጵያ