ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባ ጅፋር አቻ ተለያይቷል

በ2ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና በሜዳው ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቷል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው ሳምንት በስሑል ሽረ ከተረታው ቡድን ውስጥ ከጉዳት የተመለሱት ወንድሜነህ ደረጀ እና አቡበከር ናስርን በመጀመሪያ 11 ውስጥ ሲያካቱ በአንፃሩ ጅማ የውጭ ተጫዋቾቹን ግልጋሎት ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም በተመሳሳይ በዛሬው ጨዋታ ግልጋሎት መስጠት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም እንኳን የጠሩ የግብ እድሎች ባይሆኑም ሁለቱም ቡድኖች በተለያዩ የጨዋታ እቅዶች ገብተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ግልፅ የሆነ የማጥቃት ፍላጎት እንዲሁም ጅማዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚፈልጉ ቡድኖች መካከል ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር።

በተለይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ያልተጠቀመበት ታፈሰ ሰለሞንን በማግኘቱ በፍጥነት ወደ አደጋ ቀጠና እንዲገቡ ቀጥተኛ ቅብብሎችን በማድረግ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነበር። ሆኖም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አቤል ከበደ እና እንዳለ ደባልቄ ጥሩ የማግባት አጋጣሚዎች ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርቷል።

በግልፅ የመልሶ ማጥቃት ፍላጎት ወደ ጨዋታው የገቡት ጅማዎች ብሩክ ገ/አብ ጉልበትና በኤርሚያስ ኃይሉ ፍጥነት ላይ የተመሠረቱ መልሶ ማጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል። በተለይም ኤርሚያስ በ20ኛው እና 27ኛው ደቂቃ ላይ ያመከናቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ። በተጨማሪም በ23ኛው ደቂቃ መላኩ ወልዴ በቀጥታ ከቅጣት ምት የላካትና ለጥቂት በግቡ አናት የወጣችበት ኳስ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።

በ32ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ታፈሰ ሰለሞን ያሻገረለትን ኳስ አማኑኤል በቀጥታ በግራ እግሩ በመምታት ወደ ግብ ቢልክም የግቡን አግዳሚ ለትሞበት ሊመለሰበት ችሏል። እንዲሁም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ አስራት ያሻማውን ኳስ አቤል ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ ሊወጣበት ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው አንፃሩ በግብ ሙከራዎች እንዲሁም በእንቅስቃሴ ረገድ ደካማ ነበር።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወትሮው በተለየ በዛሬው ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ረጃጅም ኳሶች አቡበከር ናስር ወደተሰለፈበት የግራ መስመር ተደጋግመው ቢጥሉም ኳሶቹ ውጤታማ አልነበሩም።

አቡበርከር ናስር በ59ኛው ደቂቃ በጅማ ግብጠባቂ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት በፍጥነት በመድረስ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ የወጣበት እንዲሁም በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ እንዳለ ደባልቄ ከሳጥን ጠርዝ ጀምሮ ወደ ውስጥ ተጫዋቾች እየቀነሰ ከገባ በኃላ ያመነው ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው 0-0 መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና አሁንም ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ሦስተኛ ሳምንትን ሲጠበቅ በአንፃሩ ጅማ አባጅፋር ከሜዳ ውጭ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ማግኘት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: