ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ተጠባቂው የነበረው የመቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 1-1 በሆነ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ተቀራራቢ ፉክክር እና ጥሩ ጨዋታ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ከገጠመው ቡድናቸው ላውረንስ ኤድዋርድ እና ዳንኤል ደምሴን በአሌክስ ተሰማ እና አሸናፊ ሃፍቱ ተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከጅማ አባጅፋር ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስባቸው ታፈሰ ሰለሞን አስወጥተው ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃንን አስገብተዋል።

በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት እና ጥሩ ሙከራዎች በታዩበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከባለፉት ጨዋታዎች እጅግ ተሻሽለው የታዩበት እና በተሻለ ወደ ተጋጣሚ ግብ የክልል የደረሱበት ሲሆን መቐለዎች ካለፉት ጨዋታዎች በተሻለ ቀጥተኛ የማጥቃት አጨዋወት የተገበሩበት ነው።

አቡበከር ናስር ባደረገው ሙከራ የጀመረው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የደረሱበት ነበር። በመቐለዎች በኩል ከታዩት ሙከራዎች መካከል ሥዩም ተስፋዬ ያሻማትን ኳስ ያሬድ ከበደ በግንባሩ ያደረጋት ጥሩ ሙከራ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በመስመር በጥሩ ሁኔታ አታሎ በመግባት መቶ ተክለማርያም ሻንቆ እንደምንም ያዳነው ኳስ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በስምንተኛው ደቁቃም አሸናፊ ሃፍቱ ከአማኑኤል ገብረሚካኤል የተላከለትን ኳስ ይዞ ገብቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

በአጋማሹ ጥሩ የመጫወት ፍላጎት የነበራቸው እና የተጋጣሚን ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ በመግታት ጥሩ የተንቀሳቀሱት ቡናዎች ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ከሳጥን ውጭ መቶ ያደረገው ሙከራ እና ዓለምአንተ ካሣ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በአስራ ስድስተኛው ደቂቃም አማኑኤል ዮሐንስ በተከላካዮች ስህተት ያገኛትን ኳስ ለእንዳለ ደባልቄ አቀብሎት አጥቂው በጥሩ አጨራረስ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተቃራኒው ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ጊዜ ለማጥፋት በሚያደርጓቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች ታጅቦ የተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳ አጓጊ የመሸናነፍ ፉክክር ቢታይበትም ከመጀመርያው አጋማሽ በቁጥር ያነሱ ሙከራዎች የታዩበት አጋማሽ ነበር።

እንዳለ ደባልቄ በሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ አክርሮ መቶ ባደረገው ድንቅ ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ቡናዎች በአሕመድ ረሺድ እና አቡበከር ነስሩ አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም አቡበከር ነስሩ በተጋጣሚ ሳጥን በግርግር መሃል ያገኛትን ኳስ አክርሮ መቶ ፍሊፕ ኦቮኖ ያዳነበት ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር።

በባለሜዳዎቹ መቐለዎች በኩልም በጨዋታው ጥሩ በተንቀሳቀሱት አሸናፊ ሃፍቱ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል። ከሁለቱ በተጨማሪ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ሥዩም ተስፋዬ በመስመር ገብቶ ወደ ሳጥን ያሻገረው ኳስ መትቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እና ያሬድ ከበደ ተመልሶ የመጣውን ኳስ በግንባሩ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ውጤቱ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለዎች በሦስት ጨዋታ አራት ነጥብ ሲያሳኩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በዓመቱ የመጀመርያ ግባቸውን በማስቆጠር በሊጉ ሁለተኛ ነጥብ አሳክተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ