” ሠላሳ ሠባት ዓመታት ለመጠበቅ የተገደድንበት ጎል” ትውስታ በአዳነ ግርማ አንደበት

በእግር ኳስ ሕይወቱ በርካታ ድሎችን ማጣጣም የቻለው፣ ለብሔራዊ ቡድንም ወሳኝ አግልጋሎት የሰጠው ሁለገቡ ተጫዋች አዳነ ግርማ የዛሬው የትውስታ አምዳችን እንግዳ ነው።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስማቸው በግምባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አዳነ ግርማ በ1990ዎቹ መጀመርያ ወደ ሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ሁለት የፕሪምየር ሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫን ከቡድኑ ጋር አንስቶ በ1999 ክረምት ነበር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው። በፈረሰኞቹ ቤትም በዋንጫዎች የታጀበ ድንቅ አስር ዓመታት ከማሳለፉ በተጨማሪ በግሉ ሁለት ጊዜ የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ ወደ ለአፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ከረዱ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ መሆን ችሎ ነበር። ይልቁንም በኢትዮጵያ እግርኳሱ ዓለም መቼም የማይረሳ ጎል ከ37 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ያስቆጠረችው ጎል ማስቆጠር ችሏል። ለመጨረሻ ጊዜ መሐመድ ዓሊ በ1976 የአፍሪካ ዋንጫ ግብፅ ላይ ካስቆጠረ በኋላ ማለት ነው። የዚህች ታሪካዊ ጎል ባለቤት አዳነ ግርማን በትውስታ አምዳችን ልጠይቀው ወደናል።

” የማይረሳ ትውስት! ጨዋታው ነገ ሊሆን እንደዛሬ የመጨረሻ ልምምድ ሰርተን ወደ ሆቴል ስንሄድ እኔ ሳላዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ ሆነን ማነው ነገ የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ጎል የሚያስቆጥረው ስንባባል እኔ ከአጥቂ ኃላ አማካይ ስለምሆን ከሁለት አንዳችሁ ታስቆጥራላቹ ስላቸው እነርሱም አንተ አታስቆጥርም? ምነው ፈርተሀል እንዴ? ሲሉኝ ‘እኔ እንደማልፈራ ታውቃላቹ አማካይ ሆኜ ስለምጫወት እናንተ ለጎሉ ትቀርባላቹ ብዬ ነው’ አልኳቸው። ይገርምሀል ብዙ ጊዜ ከጨዋታ በፊት ፍፅም ቅጣት ምት ሲገኝ የመጀመርያ መቺ እኔ እንደሆንኩ ይነገር ነበር። የዛን ዕለት ግን አልተነገረም ነበር። ሳላዲን እንደመጠለፉ እኔ ልምታ ሲለኝ እንዳልረብሸው ብዬ ምታ አልኩት፤ ሳይጠቀም ቀረ። በተጨማሪም አንድ ለጎል የሚሆን እድል ፈጥሬለት ግን አልሆነም። ያው ፈጣሪ የፈቀደው ለእኔ ስለነበር የዚህ ታሪካዊ ጎል ባለቤት መሆን ችያለው። ጎሉን ካገባው በኃላ አዳነ ግርማ ማለት እኔ ነኝ እያልኩ ደረቴን እየመታው ወደ ደጋፊዎች ስሔድ ሳላ ቀድሞ እላዬ ላይ ሲንጠለጠል አሉላ ግርማ እና ያሬድ ዝናቡ እየሮጡ መጥተው ደስታችንን ገልፀናል። ይህ የሚያሳየው በወቅቱ የነበረንን ፍቅር እና አንድነት ነው። ጎሉ የተገኘው በህብረት ነው፤ ደስታችንንም የገፅነው በህብረት ነበር። ከምንም ነገር በላይ በሙያህ ሀገርህን ወክለህ መሳተፍ እና ሀገርህን ቀና የሚያደርግ ታሪክ መስራት በጣም ትልቅ ነገር ነው። ፈጣሪ በሰጠኝ ጉልበት ለሀገሬ ይህን በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በእግርኳስ መጫወት ከጀመርኩት ጊዜ ጀምሮ በእግርኳስ ህይወቴ ሁሌም ደስተኛ ነኝ። አንድም ቀን ፈጣሪ ረድቶኝ ከፍቶኝ አያቅም። ካዘንኩኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን አራት ውስጥ መግባት ያልቻልንበት አጋጣሚ ካልሆነ በቀር።”

አዳነ ግርማ ከፈረሰኞቹ ቤት ረጅም ዓመት በዋንጫ የታጀበ ጉዞ አድርጎ ከተለያያ በኃላ ዓምና ወደ አሳዳጊ ክለቡ ሀዋሳ በመመለስ ዘንድሮ ደግሞ ወልቂጤ ከተማን በተጫዋችነት እና በረዳት አሰልጣኝነት በስኬት እያገለገለ ይገኛል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ