ዜና ዕረፍት | የቀድሞው የኤሌክትሪክ አጥቂ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

የቀድሞ የኢትዮ ኤሌትሪክ ተጫዋች እና አሰልጣኝ እንዲሁም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ አጥቂ የነበሩት ፍቃደ ሙለታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ከስልሳዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለኢትዮ ኤሌትሪክ በአጥቂነት የተጫወቱት ፍቃደ ሙለታ በዘመናቸው ከሚጠቀሱ ጎል አዳኝ አጥቂዎች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆኑ በተደጋጋሚ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቃቸው ይታወቃል። በአሰልጣኝነት ኤሌክትሪክን ያገለገሉት እኝህ አንጋፋ አጥቂ በርካታ ተጫዋቾችን ለክለቡ አፍርተዋል። ድንቁ አጥቂ ኤልያስ ጁሀርም በእርሳቸው ሰልጥነው ለዝና ከበቁ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።

ኢትዮ ኤሌትሪክ እግርኳስ ክለብ ሲነሳ ስማቸው ቀድሞ ከሚነሱ አንጋፋ ስፖርተኞች መካከል አንዱ እንደነበሩ የሚመሰከርላቸው እኚሁ አጥቂ 1960- 77 በነበራቸው ቆይታ ቡድኑ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

አንጋፋው የስፖርት ሰው ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም በነገው ዕለት ግንቦት 25 ቀን ቀራንዮ በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሚፈፀም ይሆናል።

ሶከር ኢትዮጵያ በቀድሞው አንጋፋ ተጫዋች ሕልፈት የተሰማትን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀች ለቤተሰባቸው፣ ወዳጅ ዘመድ እና ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ትመኛለች ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ