“እናቴ ሜዳ እየመጣች ታበረታታኛለች” የሲዳማ ቡናው ተስፈኛ ተጫዋች አማኑኤል እንዳለ

ዘንድሮ በሊጉ ከታዩ ተስፈኛ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፤ የመስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ። በመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው ከተከላካይ ስፍራ እየተነሳ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፈውና ግቦችን ሲያስቆጥር የታየው ይህ ወጣት ተጫዋች የዛሬው የተስፈኛ አምዳችን እንግዳ ነው፡፡

ትውልድ እና እድገቱ በሲዳማ ዞን ለሀዋሳ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ዶሬ ባፋና ተብላ በምትጠራ አነስተኛ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ ከእግር ኳስ ጋር የተዋወቀው ግን በተወለደባት ወረዳ ሳይሆን ወደ ዶዶላ ከተማ አምርቶ ከአያቶቹ ጋር መኖር ሲጀምር እንደሆነ ይናገራል። ኳስን በአያቶቹ ቀዬ ማንከባለል በጀመረበት ወቅት ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኃላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ሲመለከት በውስጡ የተለየ ስሜት ተፈጠረና ወደ እግርኳሱ በይበልጥ እየተሳበ መጣ። በዶዶላ ቆይታው እግርኳስን በፕሮጀክት ታቅፎ ለመጫወት ጉጉት ቢኖረውም የፈለገው ሊሳካ ግን አልቻለም። ሆኖም አያቶቹ አካባቢውን ለቀው ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሀዋሳ መምጣታቸው ወደ ተጫዋችነት ለሚያደርገው ጉዞ መንገዶች ሁሉ ያማሩ እንዲሆኑለት አደረገው፡፡

ሀዋሳ ከመጣ በኋላ <<ካሱ ታዳጊ የእግርኳስ ቡድን>>ን ተቀላቅሎ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ያለመውን የፕሮጀክት ህልም እውን ቢያደርግም የተጫዋችነት ህልሙ ዕውን መሆን የጀመረው በአሻሞ ቤተሰብ ወደሚሰለጥነው የአሰልጣኝ ሰለሞን አሻሞ ቡድን ካመራ በኋላ እንደሆነ ይናገራል። “ፈጣን እንደሆንኩና እና ትልቅ አቅም እንዳለኝ ይነግረኝ ነበር። ይመክረኝ ያግዘኝም ነበር። በእግር ኳስ ህይወቴም ትልቁን ቦታ ይወስዳል።” ሲል ሁለት ዓመት በፕሮጀክት ያሰለጠነውን ሰለሞን አሻሞን ያመሰግናል፡፡

አማኑኤል ከሰለሞን አሻሞ ስብስብ ሲዳማ ዞን ልዩ ልዩ ውድድር ላይ ተሳታፊ በመሆን ለወረዳው ሲጫወት እያለ ጩኮ ከተማ ላይ የሲዳማ ቡና መልማዮች ያዩትን እና ወደ ታዳጊ ቢ ቡድን እንዲገባ ጥሪ ያደርጉለታል። ተጫዋቹም ከወረዳ አልፎ ሲዳማ ዞንን ወክሎ በመጫወት ከብዙዎች ዘንድ አድናቆት ተችሮታል፡፡ “ሲዳማ ዞንን ወክዬ ስጫወት ብዙ ክለቦች ፈልገውኝ ነበር። ጥሩ ገንዘብ እንክፈልህም ብለውኝ ነበር። ያኔ ግን በታዳጊ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ የነበረው ዘርዓይ ሙሉ ‘ቢ ቡድን እኮ ፈርመሀል፤ በአንድ አመት ውስጥ የማደግ ዕድሉ አለህ። ልጅ ነህ ወደየትኛው ክለብ አትሂድ።’ ብሎ ከለከለኝ” ሲል የሚናገረው ተስፈኛው ተጫዋች የአሰልጣኙን ምክር በመስማት የሲዳማ ቡናን ቢ ቡድን 2008 ላይ መቀላቀል ችሏል፡፡ አማኑኤል በ2008 የታዳጊ ቡድን ከተቀላቀለ በኃላ በዛኑ ዓመት በሁለት ምድብ በተከፈለው ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የደቡብ-ምስራቅ ምድብ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ አዳማ ላይ በተዘጋጀው የአጠቃላይ ውድድር ላይ ሲዳማ ቡና ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀርብ የዚህ ተጫዋች ሚና የሚዘነጋ አልበነረም።

ኳስን በአጥቂነት መጫወት የጀመረው አማኑኤል በታዳጊ ቡድን ቆይታው ከአጥቂነት ሚና ባሻገር በመስመር አጥቂነት እና በግራ እና ቀኝ የመከላከል ሚናዎችን በሚገባ ተወጥቷል፡፡ ይሁንና በመስመር ተከላካይነት ሲጫወት ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴን ማድረግ በመቻሉ በአጥቂነት ኳስን የጀመረው ተጫዋች ወደ መስመር ተከላካይነት ለመጫወት ተገደደ። እሱ ግን መጀመሪያ ላይ በዚህ ቦታ ተሰልፎ መጫወቱን ቢጠላውም የኋላ ኋላ ግን ከሚያሳየው አቋም አንፃር ቦታውን እየወደደው መጣ፡፡

በ2009 በአሰልጣኝ ዓለማየሁ ዓባይነህ (የወቅቱ የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ) ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ቢችልም ያለፉትን ሦስት ዓመታት ከቡድኑ ጋር ልምምድ ብቻ ከመስራት የዘለለ ቴሴራ ወጥቶለት መጫወት ግን አልቻለም። “ብዙ ሰዎች ቅርብ ጊዜ ያደግኩ ይመስላቸዋል። እኔ ዕድል ስላላገኘው እንጂ ካደግኩ አራተኛ ዓመቴን አስቆጥሪያለሁ። በጣም ይከብዳል የነበረው ነገር። በእግርኳስ የሚያበረታታህ ሲኖር እና ጎበዝ እየተባልክ ስታድግ ደስ ይላል። <<ቢ>> ቡድን ላይ በርካቶች ያበረታቱሀል። ዋና ቡድን ላይ አድገህ ግን ምንም ሳታደርግ ስትቀር ይከብዳል። ብቻ ግን ተምሬበታለሁ። ብዙ ጊዜዬን ቁጭ ብዬ ስላሳለፍኩ ሁሌም ፈጣሪን እለው የነበረው አንድ ቀን የምገባበትን ዕድሌን ስጠኝ ነበር። ግን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በእኔ ላይ እምነት ኖሮት ዘንድሮ ቴሴራ አውጥቶልኝ መጫወት ጀምሪያለሁ። አምናም ቴሴራ ስለሌለኝ እንጂ ልምምድ ላይ ጥሩ ነበርኩ። በምሳሌነትም እጠቀስ ነበረ። ዘንድሮ ግን ለዚህ በቅቼ በመጀመሪያ የደርቢ ጨዋታዬም ላይ ጎል አስቆጥሪዬለሁ። ያም ትልቅ ደስታን በውስጤ ፈጥሯል።”

በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ ምርጥ አቋሙን ከማሳየት ባሻገር ከመስመር ተከላካይነት ስፍራ እየተነሳ ለሲዳማ ቡና ወደ አራት ግቦችን ከመረብ ያዋሀደው ተስፈኛው በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከታዩ ድንቅ ተጫዋቾች መሀል ከመሆን በዘለለ በደጋፊውም ዘንድ በተደጋጋሚ በሜዳ ላይ ሲወደስ ይሰማል። “እኔ ስለ ሲዳማ ቡና ደጋፊ ምን ብዬ እንደምነግርህ አላወቅም፤ ቤተሰብ ነው። ሲዳማ ለኔ ትልቅ ቡድን ነው። እዚህ ቡድን መጫወት የማይፈልግ የለም። እንደ አንድ የአካባቢው ተወላጅ ወይ ሀዋሳ ነው ወይም ሲዳማ ነው መጫወትን የምትፈልገው። ያን በማሳካቴ ደስተኛ ነኝ። በመጀመሪያ ጨዋታዬ ገብቼ ጥሩ እንቅስቃሴን ሳደርግ ሁሉም ሰው ሲሰጠኝ የነበረው ሞራል እንድበረታታ አድርጎኛል” የሚለው ተጫዋቹ በመጀመሪያው አመት የሊጉ ተሳትፎው ላይ አብዛኛዎቹ ሊጉን ለመላመድ ሲቸገሩ ቢታይም እሱ ግን በቶሎ ከመላመድ ባለፈ ግቦችን ለቡድን ሲያስቆጥር አስተውለናል፡፡ “ብዙ ጊዜ ለቡድን ጓደኞቼ ወደ ሜዳ ከገባው ጎል አስቆጥራለሁ እያልኩ በድፍረት እናገራለሁ። እንደውም አንድ ጊዜ ለግብ ጠባቂያችን ፍቅሩ አዳማ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ እያደረግን ከኃላው ሆኜ ተቀይሬ ለመግባት እያሟሟኩ ‘ ከገባሁ አገባለሁ’ አልኩት። እሱም ‘ እስቲ አሳየን’ አለኝ። እንደገባሁ ጎል አስቆጠርኩ። በኔ ጎልም አሸነፍን። ጎል ለማስቆጠሬ ሚስጥሩ ደግሞ በፊት በአጥቂነት መጫወቴ ነው። ሄደር ነኝ ጎል ላይም ብዙ አልቸገርም። ፈጣን ስለሆንኩ ጎል ላይ መድረስ አይከብደኝም። ቶሎ ወደ ኃላ መመለስም እችላለሁ። ”

ከወዲሁ ፈጣን ኤድገት እያሳየ የሚገኘው አማኑኤል ስለ ወደፊት ሕልሙ እንዲህ ይናገራል። “እኔ ከአሁን በኃላ ማሳካት ምፈልገው ብሔራዊ ቡድን መጫወትን ነው። ያኔ ከ20 ዓመት በታች ጓደኞቼ ተጠርተው ሲጫወቱ በውስጤ ቁጭት ነበረብኝ። ያ ደግሞ አሁንም በውስጤ ይብሰለሰላል። በማሳየው እና ሁሉም በሚነግረኝ ምክክር ራሴን እያሻሻልኩ መጥቼ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መጫወት እፈልጋለሁ። ይሄን ደግሞ ጠብቃለሁ፤ አደርገዋለሁ። በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ፉል-ባክ ሆነው የሚጫወቱትን እመለከታለሁ፤ አድንቃቸዋለሁም። ብሔራዊ ቡድኑም በወጣት እየተገነባ እንደመሆኑ ወጣት ከመሆኔ አንፃር ያን ቦታ አስጠብቄ ለመጫወት ፍላጎቱ አለኝ። ለዛም እንደፉልባክ ነው አሁን የማስበው። ከዚህ ቀደም አጥቂ ቦታን ነበር የማልመው። አሁን በቦታዬ ደስተኛ ነኝ። ይሄን አስቀጥዬ እንደምጠራ ተስፋ አደርጋለሁ።

“እኔ እዚህ ለመድረሴ በመጀመሪያ ደረጃ ፈጣሪን አመሰግነዋለሁ። ትልቁን ነገር ያደረገልኝ እሱ ነው። ሲቀጥል በፕሮጀክት ህይወቴ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገልኝን ሰለሞን አሻሞን በጣም አመስግነዋለሁ። ተስፋ ቆርጪ ኳስን ልተው ስል ይመክረኝ ነበር። ከቤት ጭምር እያስጠራ ‘አንተ ትችላለህ፤ የቡድኔ አምበል ነህ’ እያለ ያበረታታኝ ነበር። ትልቁን ድርሻ በፕሮጀክት ህይወቴ የሚወስደው እሱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ በአሰልጣኝ ዓለማየሁ ጊዜ ባድግም ዕድሉን አላገኘሁም ነበር። ዘርዓይ ሙሉ ግን የኔን አቅም አይቶ እንድጫወት ያደረገኝ አቅሜንም አይቶ እኔ አጥቂነት ነው የምፈልገው ስለው ‘ለአንተ ፉልባክ ላይ ይሻልሀል፤ ትልቅ ደረጃ ትደርስበታለህ’ እያለ ይመክረኝ ነበር። በጣም ላመሰግነው እፈልጋለሁ። በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ትልቅ ነገር ያደረገልኝ እሱ ነው። ሌላው ደግሞ ላመሰግናት የምፈልገው እናቴን ነው። እንደ አባት እና እናት ሆና ነው ያሳደገችን። ለኳስ ያለኝን ስለምታውቅ በጣም ስለምትተማመንብኝም ነገሮችን ሁሉ ተጋፍጣልኝ ትችላህ ልጄ እያለች ላበረታችን እናቴ በጣም ነው የማመሰግናት። እናቴ አሁንም ሜዳ እየመጣች ታበረታታኛለች። እሷ በመጣችባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጎል ሁሉ አስቆጥሪያለሁ። ብቻ እናቴ ለኔ ልዩ ነች። እናትም አባትም ነች። አባቴ በዕርግጥ በህይወት አለ ከእናቴ ጋር ተለያይተው ነው የሚኖሩት። አባቴ በግብርና ላይ የተሰማራ ስለሆነ ኳስ ላይ እስከዚህም ነው።”

በአባቱ በኩል ከተወለዱት 24 ልጆች መሀል እሱ 17ኛው ልጅ ሲሆን በእናቱ በኩል ደግሞ ሁለተኛ ልጅ እንደሆነ የሚናገረው አማኑኤል ለሁሉም ወንድም እና እህቶቹ ትልቅ ቦታ እንዳለው ገልጿል። ተጫዋቹ በኮሮና በሽታ የተነሳ በቤት ውስጥ ስፖርት በመስራትም ጭምር እያሳለፈ እንደሆነ በመግለፅ ቆይታውን አጠናቋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ