ሶከር ታክቲክ | የኳስ ቁጥጥርና የመከላከል ሽግግር

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡


ታክቲካዊ ትንተና፦ በሉክ ጄጎ
ትርጉም- ደስታ ታደሰ

ኳስ ተቆጣጥሮ መጫወት በመከላከል ሽግግር ላይ ያለው ተፅዕኖ፡-

የእግርኳስ ጨዋታ እንቅስቃሴያዊ ሒደቶች በአራት ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ እነዚህም፦   የኳስ ቁጥጥር በራስ ቡድን ስር ሲሆን (…In Possession)፣ የኳስ ቁጥጥር በተቃራኒ ቡድን ስር ሲሆን (…Out of Possession)፣ ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግር (Defending Transition) እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግር (Attacking Transition) ናቸው፡፡ በዘመናችን እግርኳስ የታክቲክ ጠቢብ የሆነው ፔፕ ጋርዲዮላ እንዳለው አራቱ የእግርኳስ ቅጽበቶች (Moments) እጅግ ተያያዥና አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጉልህ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ይህም የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስደው የሚጫወቱ ቡድኖች በተጋጣሚዎቻቸው ጫና ኳስ ቢነጠቁ አልያም ቢያጡ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚያርፍባቸው ቀድመው ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ይህ ታክቲካዊ ትንተና ኳስ በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉ ቡድኖች ኳሱን ባጡበት ቅጽበት ስኬታማ ሽግግር ለመከወን የሚጠቀሙዋቸውን ታክቲካዊ መፍትሄዎች ያብራራል፡፡ የታክቲካዊ ንድፈ ሃሳቡ ዝርዝር በኳስ ቁጥጥር የተካነ ቡድን ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ይዳስሳል፡፡


በሜዳ ቁመት የሚደረግ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ ጥግግት (Vertical Compactness)፦

አንድ ቡድን ኳስ ሲይዝ ምን አይነት የጨዋታ ዘይቤ መከተል እንዳለበት የሚያቅደውን ያህል ቡድኑ ኳስ ሲያጣም እንዴት መጫወት ወይም መከላከል እንደሚኖርበት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አሰልጣኙ ይህን ጉዳይ በጥልቁ ሊያስብበት ይገባል፡፡ በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይ የሚፈጠር አልያም በቀላሉ የሚገኝ ክፍት የመጫወቻ ቦታ (Space) ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህ ክፍተት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በያዘው ቡድን ተጫዋቾችም ሆነ በተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ ውሳኔ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ አንድ ቡድን የቱንም ያህል ጠንካራ የማጥቃት ሒደት ያከናውን  በሚያጠቃበት ዘዴ ወይም ሥልት ሳቢያ ክፍተትን መፍጠሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ተጋጣሚ ቡድንን የምናጠቃበት መንገድ በተቃራኒው የራሳችን የመከላከል ሽግግር ላይ እክል ያመጣል፡፡ 

ለምሳሌ፡- በከፍተኛ ፍጥነት የመልሶ ማጥቃት የሚተገብር ቡድን በአብዛኛው በሜዳው ቁመት በመከላከል ሲሶው ላይ ክፍተቶችን ይፈጥራል፡፡ ለመልሶ የመጠቃት ሒደትም ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ይህ የሚከሰተው በመልሶ ማጥቃት የሚጫወተው ቡድን ተከላካዮች ኳስ የነጠቀውን እና በፈጣን ሒደት የመልሶ-ማጥቃት ለመተግበር የተዘጋጀውን ተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ፍጥነት የሚቋቋሙበት አደረጃጀት ላይ በቀላሉ መገኘት ስለሚያዳግታቸው ነው፡፡ በተለይ በመላው ተጫዋቾቻቸው ለሚያጠቁ ቡድኖች የሽግግር ሒደቶች ከባድ ይሆንባቸዋል፡፡ ከታች የተመለከተውና በ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ላይ አስገራሚ ቡድን ሆኖ የቀረበው የሜክሲኮ ብሔራዊ ቡድን በፍጥነት የሚያጠቃ ቢሆንም ተጫዋቾቹ ኳስ ሲነጠቁ በቶሎ የተሳካ ሽግግር አድርገው ኳስን ለማግኘት ሲቸገሩ  እንደነበር ያመለክታል፡፡ ይህ ድክመት የሚከሰተው በመስመሮች መካከል በሚፈጠር ከፍተኛ ክፍተት እንደሆነ ምስሉ ያሳያል፡፡ ስለዚህም ኳስ እግሩ ሥር የያዘው የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ኳሱን ተቆጣጥሮ ብዙ ጊዜ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡በተጨማሪም ኳስ የያዘውን ተጫዋች በቅርበት ሆኖ የመቀባበያ አማራጭ ለማሳጣት የሚሞክሩ በሽግግር ሒደት ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ጥቂት ብቻ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ኳስ የያዘው ተጫዋች በተለይ ወደ ተጋጣሚ ቡድን የመከላከያ ክልል በርካታ የመቀባበያ መስመሮች እንዲያበጃጅ ሰፊ ቦታ እና በቂ ጊዜ ያገኛል፡፡

በሜዳ ላይ የመቀባበያ አማራጭ መስመሮች ሲበዙና ይህን ለማሰብ በቂ ቦታ ሲገኝ ተጋጣሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር አመቺ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህም ከማጥቃት ወደ መከላከል የተሳካ ሽግግር ከውኖ ኳስን በፍጥነት በራስ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ የሚወጥኑ ቡድኖች በሜዳው ቁመት በተጫዋቾቻቸው መካከል የሚፈጠረውን እንቅስቃሴያዊ ወይም ዋላይ ርቀት እጅግ ማጥበብ ይኖርባቸዋል፡፡ በተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን በዲፓርትመንቶቹም  ማለትም በተከላካይ ክፍሉና በአማካዩ፥ በአማካይ ክፍሉና በአጥቂው መካከል የሚኖረው ጥግግት በደንብ የተሰራበት መሆን አለበት፡፡ ይህ የጥግግት  አይነት በሚከተለው ምስል የባርሴሎና ቡድን ለፍጹምነት በተጠጋ ልክ ሲተገብረው እንደነበር ይታያል፡፡ በምስሉ በማይታየው የተከላካይ ክፍሉ እና የአጥቂ ክፍሉ መካከል ያለው ርቀት በጣም አጭር ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ቡድኑ ሁለት መሰረታዊ ጥቅሞችን ያገኛል፡፡ የመጀመሪያው በመስመሮች መካከል የሚፈጠረው ክፍተት እጅግ ጠባብ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቡድኑ ተጫዋቾች እና በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች መካከል የሚኖረውም ክፍተት እንዲሁ ጠባብ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ኳስ የያዘን ተጫዋች ተጭኖ ለመንጠቅ (Press-ለማድረግ) ይረዳል፤ ያኔ ቡድኖች የተጭኖ መጫወት ታክቲኮችን (Pressing Tactics) መተግበር ይጀምራሉ- እንደ <Cover Shadow> አይነቱን ማለት ነው፡፡

በሜዳ ስፋት የሚደረግ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ የጎንዮሽ ጥግግት (Horizontal Compactness)፦
በእግርኳስ መጫወቻ ሜዳ ላይ በተጫዋቾች መካከል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ሊያጠብ የሚያስችል ሌላኛው ንድፈ ሐሳባዊ እንቅስቃሴ የአግድሞሽ ጥግግት (Horizontal Compactness) ነው፡፡ አንዳንድ ቡድኖች ክፍተቶችን ለመድፈን አጥብበው እንደሚከላከሉት ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ ሊያጠቁም ይችላሉ፡፡በሜዳው ስፋት የአግድሞሽ ጥበት ያለባቸውን ፎርሜሽኖች በመጠቀም ኳስን ወደ ተጋጣሚ የመከላከያ ክልል ጋር በማድረስ በሽግግር ወቅት የሚፈጠሩ ክፍት ቦታዎችን መቀነስ ያስችላል፡፡
ከታች በቀረበው የሬድ ቡል ላይብዚሽ የጎንዮሽ ጥግግት ምስል እንደሚታየው ላይብዚሾች በሜዳው የመሃል ክፍል ሰባት ተጫዋቾች ይኖራቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አማካይ ክፍላቸው በዳይመንድ ቅርጽ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ አደራደር ሲጫወት የአማካዮቹ ቁጥር ስምንት ይደርሳል፡፡ ስለዚህም ኳሱን በመሃለኛው የሜዳ ክፍል በሚደረግ ሽግግር ኳስ ሲነጠቁ መልሶ ኳሱን ለማግኘት እርስ በእርሳቸው ቅርብ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ምንም እንኳ ለቡድኑ የጎንዮሽ ስፋት የሚጨምሩ  ሁለት ተጫዋቾች ቢኖራቸውም እነርሱም ቢሆኑ መስመሮቻቸውን ታከው የሚጫወቱትና የተለመዱት አይነት የመስመር አማካዮች አይደሉም፡፡

በካርሎ አንቼሎቲ ሲመራ የነበረው ባየር ሙኒክን የተመለከተው ታክቲካዊ ትንተና ከላይ ከቀረበው በመጠኑ የተለየ አቀራረብ ያሳያል፡፡ ባየርኖች አብዛኛውን ጊዜ በመስመሮቻቸው ላይ በፍራንክ ሪቤሪ እና በአሪያን ሮበን አማካኝነት ወደፊት ተጠግተው እንዲሁም ወደ ጎን አስፍተው  ይጫወታሉ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ፊሊፕ ላህም እና ዴቪድ አላባ ተጨማሪ ስፋትን ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ ይህም ለባየርኖች ሜዳውን በስፋትም ሆነ በቁመት የመለጠጥ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ በምስሉ ላይ የሚታየው ተጋጣሚያቸው ሪያል ማድሪዶች ግን ኳስን ባሻቸው ልክ እንዳያንሸራሽሩ ርቀቱ በዝቶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሽግግር ወቅት ባየርን ሙኒኮች ረጅም ርቀትና ሰፊ ቦታ ለመሸፈን እንደሚገደዱ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፦ ከታች በተመለከተው ምስል ሮበን በሜዳው የላይኛው ክፍልና በመስመሩ አስፍቶ ሲጫወት ይታያል፡፡ሪቤሪም ቢሆን ተመሳሳዩን ለማድረግ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ በምስሉ አርቱሮ ቪዳል የረጅም ኳስ ቅብብል ለመከወን ሲጥር በማርሴሎ ሲቋረጥበትም እናያለን፡፡ ባየርኖች በሚፈጥሯቸው ክፍት ቦታዎች ሳቢያ ይህ የኳስ መቋረጥ በተፈጠረበት አካባቢ ሌሎች ተጫዋቾች ስለሌላቸው የመልሶ ማጥቃት ወይም ኳሱን መልሶ የማግኘት ሒደት ውስጥ ሲገቡ አይታዩም፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡