ስለ ዐቢይ ሃይማኖት (አስቴር) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

የንግድ ባንክ ምልክት ተደርጎ የሚቆጠረው እና ሰው በሰው የመያዝ የመከላከል መንገድ በሚተገበርበት በዚያ ዘመን አጥቂዎችን በተገቢ ሁኔታ በመቆጣጠር የሚታወቀውና ከዘጠናዎቹ ምርጥ ተከላካዮች መካከል አንዱ የሆነው ዐቢይ ሃይማኖት ማነው?

አልማዝዬ ሜዳ ላይ በተደረገ የታዳጊዎች ምርጫ በታላቁ የእግርኳስ ሰው መንግሥቱ ወርቁ አማካኝነት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ተመርጦ ተጫውቷል፤ የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ እንግዳችን ዐቢይ ሃይማኖት። ዐቢይ ትውልዱ አዳማ (ናዝሬት) ከተማ ቢሆንም ያደገው በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ አቧሬ (ቤሌር ሜዳ) አካባቢ ነው። በቀደመው ጊዜ አባቱ በድሬደዋ እና በሐረር በተከላካይ ቦታ ተጫውተው ማለፋቸው እና እርሳቸውን በማየት እርሱ ወደ እግርኳሱ ተስቦ እንደገባና ከፍተኛ ፍላጎት እንዳደረበት ይነገራል። በእርሱ በቻ ያላቆመው እግርኳስ ተጫዋችነት ፍላጎት በወንድሞቹ ተጋብቶ በፀሎት እና ፍፁም ሐይማኖት በትልቅ ደረጃ ባይሆንም እግርኳስን ተጫውተው አልፈዋል።

ከቤታቸው ፊት ለፊት በ1970ዎቹ የተጫወተው የቀድሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሐል ተከላካይ ሰለሞን መንገሻን እያየ ያደገው ዐቢይ እርሱ በሚጫወትበት ቦታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት በነበረው ከፍተኛ ፍላጎት በ1982 እና 83 ለሁለት ዓመት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቷል። አጭር ጊዜ ቢሆንም ጣፋጭ የእግርኳስ ህይወት ያሳለፈበት ሜታ አቦን በ1984 ካገለገለ በኃላ ለዘጠኝ ዓመታት ወደተጫወተበት እና ትልቅ ስምና ዝና ወዳአፈራበት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊገባ ችሏል። ንግድ ባንክ የገባበት መንገድ አስገራሚ ያደርገዋል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ የማይረሳው ኢራቅ ሀገር ሔዶ በወዳጅነት ጨዋታ አስራ ሦስት ለዜሮ የተሸንፈው የንግድ ባንክ ቡድን ውስጥ ሳይፈርም ከቤቱ ወደ ኢራቅ ወስደው እንዲጫወት አድርገውት ሲመለስ አውሮፕላን ውስጥ እያለ ለንግድ ባንክ ብትጫወት ለብሔራዊ ባንክ ሠራተኛ እና ተጫዋች ትሆናለህ የተሻለ ጥቅም ታገኛለህ በሚል ማማለያ አቅርበውለት በዚህ በመስማማት ነው ንግድ ባንክ ሊገባ የቻለው።

በብሔራዊ ቡድን እና ቤሌር ሜዳ በአንድ ሠፈር ውስጥ አብሮት ሲጫወት የቆየው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የአሁኑ የጅማ አባ ጅፋሩ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ማንጎ ስለ ዐቢይ እንዲህ ይናገራል። “በጣም ጠንካራ ተከላካይ ነው። ዕልሁ፣ ወኔው አልሸነፍ ባይነቱ ደስ ይል ነበር። የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ ጥሩ የሚባል፣ የመጫወት ፍላጎቱም ቢሆን ከፍተኛ የነበረ ተከላካይ ነው።”
በኢትዮጵያ እግርኳስ ቤተሰብ ዘንድ መቼም የ1987 የባንክ ቡድን አይረሳም። አስራ አራተኛው ሳምንት ሰማንያ ሰባተኛው ደቂቃ ድረስ ውድድሩን እየመራ ነበር። የዋንጫውን አንድ እጀታ ይዟል ማለት ይቻላል። ንግድ ባንክ ሦስት ዕድሎች ይዞ ወደ ሜዳ ገብቷል። ማሸነፍ፣ ነጥብ መጋራት እንዲሁም ከሁለት በላይ ጎል ሳይቆጠርበት መሸነፍ። በዚህ ሁሉ ዕድል ውስጥ ድራማዊ በሆነ ትዕይንት 87ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ ከበደ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በፈረሰኞቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቆ ንግድ ባንክ ዓመቱን ሙሉ የለፋበትን ዋንጫ ማጣቱ መቼም የሚዘነጋ አይደለም። በዚህ ቡድን ውስጥ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ዐቢይ ሃይማኖት ነበር።

ብዙዎች ፀጉሩን አሳድጎ በረጅሙ በመሰራቱ (dreadlok) ይመስላል ከዋናው ስሙ ይልቅ ‘አስቴር’ በማለት በቅፅል ስሙ የሚጠሩት ይህ ድንቅ ተከላካይ ከንግድ ባንክ ዘጠኝ ዓመታት አገልግሎት በኃላ እግርኳስን ከማቆሙ በፊት ለተወሰኑ ዓመተታት በኒያላ ተጫውቶ በ1994 እግርኳስን ሊያቆም ችሏል። በብሔራዊ ቡድን አብሮት እንዲሁም በእርሱ በተቃራኒ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በወቅቱ ይጫወት የነበረው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ስለ ዐብይ ሐይማኖት ይህን ብሎናል። “በጣም ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ የሆነ የግንባር ኳስ የሚገጭ ጎበዝ ተከላካይ ነው። በቦታው ሁሉን ነገር ጠብቆ የሚጫወት፣ ከኃላ ሆኖ ቡድን የሚመራ ፣ ማድረግ ያለበትን ሁሉ በትክክል የሚያደርግ ጎበዝ ተከላካይ ነው”።

አሰልጣኝ ካሣሁን ተካ በያዘው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በተለያየ ጊዜ ተመርጦ ለብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት የሰጠው ዐብይ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ ከአስር ዓመት በላይ ሆኖታል። ይህን የዘጠናዎቹን ኮከብ ካለበት ሀገር አሜሪካ አፈላልገን በስልክ አግኝተነው እርሱም ይሄን ነግሮናል።

” በመጀመርያ ፈልጋቹ አግኝታችሁ ስላቀረባችሁኝ ከልብ አመሰግናለው። እውነት ልትከበሩ ይገባል። እኔ ስኬትን የምመለከተው አንድ ጠቅለል ካለ ሀሳብ ነው። ይሄም ማለት ምንድነው በሠላም የከፋ ጉዳት ሳይደርስብኝ እስከምፈልገው ድረስ ተጫውቼ በማሳለፌ ፈጣሪን አመሰግናለው። እንደትልቅ ስኬት ነው የምቆጥረው። በክለብም በብሔራዊ ቡድንም በትልቅ ደረጃ ተጫውቶ በመልካም ጤንነት መጨረስ ትልቅ ነገር ነውና ይሄንን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

“በእግርኳስ ህይወቴ የሚቆጨኝ ነገር ያው በ1987 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለዋንጫ ደርሰን ዋንጫ ያጣንበት ጊዜ ነው። እስካሁን ድረስ ለምን እንደሆነ አይገባኝም። ቀድመን ጎል አስቆጥረን ጨዋታውን ከተቆጣጠርን በኃላ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም። ብቻ ትልቅ ቁጭት የሚፈጥር ነው። ዋንጫ ለማንሳት የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሰን ዋንጫ ማንሳት ሲገባን ያው በተለይ የሙሉጌታ ከበደ ብልጠት ቡድኑን የበለጠ ጠቅሞት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫን ሊያነሳ ችሏል። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ብዙ ስህተቶች ነበሩን እንዴት ጨዋታውን ተቆጣጥረን ውጤት ማስጠበቅ እንደነበረብን ያንን የመረዳት አቅም(ብስለት) ባለመኖሩ ውጤታችንን አሳልፈን ሰጥተናል። ያው በጣም የሚቆጨን አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ከዚህ ውጪ እግርኳስን ጠግቤ በመጫወት እስከፈለኩት ጊዜ ድረስ መጫወት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ ።

“በኢራቅ ሀገር አሰራ ሦስት ለዜሮ የተሸነፍንበት ጨዋታ በጣም የሚገርም በታሪክ ተመዝግቦ የተቀመጠ ነው። ብዙ ጎል ነው የተቆጠረው። ዋናው ምን መሰለህ ያ ቡድን የባንክ ቡድን አይደለም። የባንክ ዋናው ጠንካራው ቡድን አልነበረም። ለብሔራዊ ቡድን እና ለሆነ ጨዋታ ጭምር ተከፋፍለው ወደ ኤርትራ የሄዱ ተጫዋቾችም ነበሩ። የክለቡ አመራሮች የተለያዩ ተጫዋቾችን በውሰት አሰባስበውን ነው የመጣነው። አስታውሳለው በ1984 ክረምት ላይ ነው ሜታ እየተጫወትኩ እረፍት ባለሁበት ሰዓት ከቤት መጥተው የወሰዱኝ። ገና እኛ አልፈረምንም ዝም ብለው ወስደው ደብረዘይት ክትፎ እያበሉን ማዘጋጀት ጀመሩ። እኛም ብዙም ሳንዘጋጅ እንዲያውም ክረምት ስለነበረ ሜዳ ሁሉ አጥተን ልምምድ ለመስራት እንቸገር ነበር። ይሄንን አቅም ይዘን ነው ወደ ኢራቅ የሄድነው። በጣም ብዙ የጎል ውርጅብኝ ነው የወረደብን። በጣም ከአቅማችን በላይ ነበር። በተለይ የኢራቅ የነበረውን ሁኔታ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው በወቅቱ የነበሩ የቡድኑ አመራሮች ይሄንን ውድድር መቀበል አልነበረባቸውም። ቡድኑ ያለበትን ክፍተት በመረዳት ይህን ውድድር ባይቀበሉ እመረጥ ነበር። ጠንካራ ቡድኖች ነበሩ እዛ ሄደን ያጋጠሙን። ከኢራቅ ቡድን ባለፈ የኮንጎ እና የአልጄሪያ ቡድኖች ነበሩ። ይህ ዕድል ሲመጣ ‘በቂ ዝግጅት ሳናደርግ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች በሌሉበት እነዚህ በውሰት ያመጣናቸው ተጫዋቾች አሰባስበን ምን ዓይነት ውጤት ልናመጣ ነው ? ‘ በሚል ጥናት አጥንተው በጥቅሙ እና በጉዳቱ ዙርያ ተነጋግረው ባለመሄዱ ተስማምተው መቀረት እየተቻለ እንደው ሄድን ለማስባል ብቻ የወሰኑት ትልቅ ስህተት ነው።

“አስቴር የሚለው ቅፅል ስም ብዙም አያስጨንቀኝም። ምክንያቱም እኛ እግርኳስ ስንጫወት ተመልካቾች የተለያየ ስም አውጥተው ሲጠሩህ ያው ሊዝናኑ ነው የሚገቡት አንተ ደግሞ ልትዝናና ነው የምትገባው። ተመልካቹ ደግሞ ተዝናንቶ በፈለገው ስም ይጠራሀል። ምንም የምታደርገው ነገር የለም። ለእኔ የሚሰጠኝ ብዙም ዓይነት ነገር የለውም። ካስደሰታቸው በዚህ ሊጠሩ ይችላሉ። ለእኔ ግን ብዙም የሚሰጠኝ ስሜት የለም።

“የባንክ ቡድን መፍረስ በሰማሁ ጊዜ በጣም ተሰምቶኝ ነበር። በኃላ ላይ በምን ምክንያት እንደፈረሰ ማወቅ ግን ይገባል። ምክንያቱም የትኛውም ክለብ ሊፈርስ ይችላል። ግን የፈረሰበት ምክንያት አጥጋቢ ሊሆን ይገባል። እግርኳሳችን ብዙ ጊዜ በዚህ ሙያ ላይ ዕውቀት እና ፍላጎት በሌላቸው ሰዎች ስለሚመራ ትንሽ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር አይፈጠርም ማለት የዋህነት ነው። በዚህ ምክንያት ባንክ ሊፈርስ ችሏል። መፍረስ አልነበረበትም። ብዙ ማስተካከያ አድርጎ መቀጠል ይቻል ነበር። እግርኳስ ላይ ብዙ ክስተቶች ይፈጠራሉ መውጣት መውረድ ሁሉ ነገር ያለ ነው። ግን ይሄን መረዳት ያስፈልግ ነበር። ይህን መረዳት በማያቁ ሰዎች እግርኳሱ በመመራቱ ባንክ ሊፈርስ ችሏል። በተረጋጋ ሁኔታ ከስሜት በመውጣት መፍትሔ በመስጠት ወደተሻለ አቅጣጫ ክለቡን ማስኬድ እየተቻለ መፍረሱን ያሳዝናል። እኔ በዚህ ሁኔታ ነው የምመለከተው።

“በአሰልጣኝነቱ ረጅም ርቀት ሄጃለው። አሁን ወቅት በምኖርበት ቴክሳስ ከተማ Classic soccer Academy Of Gretar Houston የተሰኘ አካዳሚ በቅርቡ እከፍታለው። በዚህ ዓመት ትልቅ ዕቅድ ነበረኝ። ከቴክሳስ ከተማ የአካዳሚ መክፈት የሚያስችል ሰርተፍኬት ለመውሰድ ብዙ ፈተናዎች ነበሩ። ከአራት እስከ አስራ ስምንት ዓመት ድረስ ያሉ ታዳጊዎችን ለማሰልጠን ፕሮሰሱን ጨርሼ፣ ሜዳም አግኝቼ ብዙ ነገሮች ከሄድኩ በኃላ የወቅቱ በሽታ ስለመጣ እንቅፋት ሆኖብኛል። ዞሮ ዘሮ ከመጀመር ወደ ኋላ አልልም። ፈጣሪ ከፈቀደ ከዚህ በሽታ በኃላ እጀምራለው ብዬ አስባለው።

“ኑሮዬን በአሜሪካ ካደረኩ ረጅም ዓመት ሆኖኛል። ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። ባለቤቴ ሄለን ኢብራ ትባላለች ወንድ ልጄ ራአፋኤል፣ ሴት ልጄ ኤልዳና ትባላለች። ወንዱ ልጄ ምንም ዓይነት የኳስ ፍቅር የለውም። ዝንባሌው ቅርጫት ኳስ ነው። ይሄ ደግሞ ፍላጎቱ ነው። ፍላጎቱን መግታት አይቻልም። ባይሆን ሴት ልጄ ግን እኔን የመከተል ፍላጎት ኖሯት በመለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እግርኳስ ትጫወታለች። በጣም የሚገርመኝ የመጫወት ፍላጎቷ በመከላከል ባህሪ ውስጥ መሆኑና ከእኔ ጋር መመሳሰሉ በጣም ነው። ይገርምሀል አባቴም እግርኳስ ተጫዋች በነበረበት ዘመን ተከላካይ ነበር። እንድያውም ባለፈው የኢትዮጵያውያን የስፖርት ውድድር ላይ ፍስኃ ወልደአማኑኤልን አግኝቼው ከእርሱ ጋር አብሮ ተጫውቷል። አባቴ ወደ መጨረሻው ኳስ ማቆሚያ ወቅት ተጫዋችም አሰልጣኝም ሆኖ እንዳለፈ ብዙ ነገር አጫውቶኛል። በወቅቱ ጠንካራ ተከላካይ እንደነበር እሰማለው። እኔም ሳላቀው እርሱን ተካሁት መሰለኝ የአባቴን መንገድ ተከትዬ ተከላካይ ሆኜ ተጫውቻለው። በጣም የሚገርመው ሴት ልጄ ኳስ ስትጫወት ተከላካይ መሆኗ ነው። ፍላጎቷ ጥሩ ነው ከበረታች ትልቅ ደረጃ ትደርሳለች በዬ አስባለው። በመጨረሻም ለሀገሬ በእግርኳሱ አንድ ነገር አደርጋለው ብዬ ብዙ ያቀድኳቸው ዕቅዶች አሉኝ። ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገር በቀጣይ ዓመት ወደ ሀገሬ በመምጣት የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት አስባለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ