አማኑኤል ተሾመ ወደ ቀድሞ ክለቡ አምርቷል

ላለፉት ቀናት በወልዋሎ የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ የነበረው አማካዩ አማኑኤል ተሾመ ወደ ቀድሞ ክለቡ ወላይታ ድቻ በድጋሚ ተመልሷል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት መከላከያን ለቆ ወደ ድሬዳዋ ከተማ በማምራት የመጀመርያውን ዙር ከብርቱካናማዎቹ ጋር ያሳለፈው ይህ አማካይ ባለፈው ሳምንት ቀሪ የስድስት ወር ውል እያለው ነበር ከክለቡ ጋር በስምምነት የተለያየው። ከቀናት በፊት ወደ ዓድግራት በማምራት ከወልዋሎ ጋር ሙከራ እያደረገ የነበረው ይህ የቀድሞ መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ አማካይ በ2008 እና 2009 ወዳሳለፈበት ወላይታ ድቻ በድጋሚ ለማምራት ተስማምቷል።

ክለቡ ከቀናት በፊት በአማካይ ስፍራ ከወልዋሎ ጋር የተለያየው ሚካኤል ለማን ማስፈረሙ ሲታወስ የሁለቱ መቀላቀል የአማካይ ክፍሉን ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ወላይታ ድቻ በዝውውር መስኮቱ እስካሁን መሐመድ ናስር፣ አማኑኤል ተሾመ፣ ሚካኤል ለማ እና አበባው ቡታቆን ማስፈረም ችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ