ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በድል ጎዳናው ቀጥሏል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በድል ጎዳናው ቀጥሏል

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን አርባምንጭ ከተማን 2ለ0 አሸንፎ ተከታታይ ሦስተኛ ድል በማስመዝገብ ልዩነቱን ወደ 11 ነጥቦች አስፍቷል።

አዞዎቹ ነጥብ ተጋርተው ከመጡበት ከባለፈው ሳምንት ጨዋታቸው አምስት ተጫዋቾች ቅያሪ አድርገዋል። ፀጋዬ አበራ አሸናፊ ፊዳ ቡታቃ ሸመና፣ ፍቃዱ መኮንን እና አህዋብ ብሪያንበተመስገን ኤልያስ፣ ካሌብ በየነ፣ መሪሁን መስቀለ፣ እንዳልካቸው መስፍን እና አህመድ ሁሴን ሲተኩ ኢትዮጵያ መድን ድል ካደረገው ስብስቡ በታዬ ጋሻው ምትክ አዲስ ተስፋዬ በብቸኝነት ለውጠዋል።

ፌደራል ዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ በመሩት ጨዋታ በሁለቱም በኩል ዒላማውን የጠበቀ የጠራ የጎል ሙከራዎች ለመመልከት አዳጋች የነበረ ቢሆንም የጨዋታውን ሚዛን ለመቆጣጠር እና ክፍት ቦታችን ለማግኘት ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ጨዋታውን እንዳይቀዛቀዝ አድርጎት የውሃ ዕረፍት ደርሷል።

በመጀመርያዎች ሃያ አምስት ደቂቃዎች ከተመለከትነው እንቅስቃሴ ዕምብዛም የተለየ ነገር ባይኖርም ሁለቱም ጋር ከኳስ ጋር ምቾት ተሰምቷቸው የተሳኩ ቅብብሎሽ በማድረግ የሜዳው ሦስተኛ ክፍል ቢደርሱም በማጥቃቱ በኩል መሳሳት የነበራቸው በመሆኑ 36ኛው ደቂቃ መሐመድ አበራ ከግራ መስመር ተሻግሮለት በግንባሩ የገጨው እና ግብጠባቂው ኢድሪስ በቀላሉ ከያዘበት ያልተሳካ ሙከራ በቀር ሌላ የተለየ ነገር ሳንመለከት አጋማሹ ተገባዷል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ በሁለቱም በኩል በይበልጥ ማጥቃቱ ተሽለው ሲቀርቡ በሁለት አጋጣሚ ጠንካራ ሙከራዎችን አድርገዋል። በኢትዮጵያ መድን በኩል 46ኛው ደቃ ዳዊት ተፈራ ከቀኝ የሜዳው የመሐል ክፍል አንስቶ ኳሱን እየገፋ በመሄድ ከርቀት የመታው እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት እንዲሁ በአዞዎቹ 52ኛው ደቂቃ ይሁን እንደሻው ከመሐል ሜዳ ተከላካይ በመቀነስ ወደ ፊት በመሄድ የመታው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

በእነዚህ ሁለት ሙከራዎች ጨዋታውን ከፍ ወደ አለ ፉክክር እንዲያመራ አድርጎት ኢትዮጵያ መድኖች የመጀመርያ ጎላቸውን 58ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጠረዋል። በየጨዋታዎች ለጎሎች መቆጠር ምክንያት በመሆን ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ያሬድ ካሳይ ተከላካይ በማለፍ ያሻገረውን ከጀርባ የመጣው በረከት ካሌብ በግንባሩ ሲገጨው ግብ ጠባቂው ኢድሪስ ሲመልሰው ያገኘውን ኳስ አለን ካይዋ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

አርባምንጮች በደቂቃዎች ልዩነት የአራት ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ በሚያስቡበት ወቅት ከፍተውት የሚሄዱትን ቦታ የበለጠ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የተጠቀሙበት መድኖች ረመዳን የሱፍ በ83ኛው ደቂቃ ከፈጠረው አደገኛ ሙከራ እንዲሁም ዳዊት ተፈራ አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂው ኢድሪስ ኦጎዶጆ ካወጣባቸው የሚያስቆጭ ተከታታይ ሙከራ በኋላ ሁለተኛ ጎላቸውን 88ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ወገኔ ገዛኸኝ ከሜዳው ቀኝ ክፍል ያሻገረለትን አቡበከር ሳኒ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 2-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።