ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና

በደረጃ ሰንጠረዡ በአምስት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እና ሲዳማ ቡናዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል ለማድረግ የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው።

በሰላሣ ሁለት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች ለማገገምና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ድል እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው ዙር በብዙ ረገድ መዳከማቸውን ተከትሎ ደረጃቸው አሽቆልቁሎ ለወራጅ ቀጠናው እጅግ ተጠግተዋል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ዘጠኝ ጨዋታዎች ስድስት ሽንፈት፣ ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ መገኘቱ ከሰንጠረዡ አካፋይ ለመሻገር ከነገው ጨዋታ ድል እና ድል ብቻ እንዲያልም ያደርገዋል።
ኤሌክትሪኮች በቅርብ ሳምንታት በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የታዩባቸው ጉድለቶች በውድድሩ ወሳኝ ወቅት ላይ ከጨዋታዎች በቂ ነጥብ እንዳይሰበስቡ አድርጓቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ አስቆጥሮ ስምንት ግቦች ማስተናገዱም በፊት እና ኋላ ክፍሎች ያሉበትን ችግሮች ማሳያ ሲሆን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሰውን ሲዳማ ቡና በሚገጥሙበት የነገው ጨዋታም ድክመቶቹን አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል። በተለይም የመከላከል ክፍሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በጥሩ ብቃት ላይ ለሚገኘው የተጋጣሚው የፊት ጥምረት በሚመጥን አኳኋን ወደ ጨዋታው መቅረብ ግድ ይለዋል።  የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድን ከነገው ፍልምያ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻለ ከስጋት ቀጠናው በመራቅ መጠነኛ እፎይታ እንዲያገኝ ያስችለዋል፤ ይህም ለጨዋታው ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ በጥንቃቄ እንዲከውን ያደርገዋል።

በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ሁለት የአቻ ውጤቶች መልስ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ይገጥማሉ።

ድንቅ ፍልሚያ በታየበት የመጨረሻው ሳምንት መርሐ-ግብር ከመቻል ጋር ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ማግኘት ባይችልም ጠንካራ ጎኖቹ በድጋሚ በእንቅስቃሴው ውስጥ ታይተዋል። ባህርዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና የመሰሉ ጠንካራ ቡድኖች አሸንፎ ካሳካቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በተከናወኑ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ቢችልም በእንቅስቃሴ ረገድ አሁንም በጥሩ ብቃቱ የዘለቀው ሲዳማ ቡና ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ በመጨረሻው መርሐ-ግብር የነበረው ቀዝቃዛ አጀማመር እንዲሁም ውስን የመከላከል ድክመት ማረም ይኖርበታል። ቡድኑ ከቀዝቃዛው አጀማመር በማገገም ከመመራት ተነስቶ ጨዋታውን እስከ ከመምራት መድረሱ እንዲሁም በጠንካራው ጨዋታ ያሳየው የማሸነፍ መንፈስ የሚደነቅ ቢሆንም በአራት መርሐ-ግብሮች አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ ወደ ጨዋታው የቀረበው የተከላካይ ክፍሉ የነበረው ብቃት ግን መሻሻል የሚገባው ነው።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በሲዳማ ቡና በኩል አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስን በቅጣት ከማጣታቸው ውጭ የተሟላ ስብስባቸውን ይዘው ይቀርባሉ።

ቡድኖቹ እስካሁን 21 ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 8 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ሲዳማ ቡና 5 አሸንፎ በ 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ኤሌክትሪክ 19 ሲዳማ ቡና ደግሞ 17 ጎሎችን አስቆጥረዋል።