የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የስፖርታዊ ጨዋነት ባለ ድሉ ቦሌ ክፍለ ከተማ!
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2017 የውድድር ዘመን ከቀናት በፊት ለተከታታይ አምስት ዓመታት ባሳካው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የበላይነት መቋጫውን ማግኘቱ ይታወሳል። በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት የሚስተካከለው እንደለሌው ሁሉ በየዓመቱ በውድድሩ ላይ እያስገረመን የመጣ አንድ ቡድን ደግሞ ለተከታታይ አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫን በማሳካት ለብዙኀን ግንባር ቀደም ምሳሌ ሆኗል።
ከአራት ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ብቅ ካለ በኋላ በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን በመያዝ በሊጉ ላይ አስደናቂ እንቅስቃሴን በማሳየት ለበርካታ ተመልካቾች አዝናኝ እግር ኳስን የሚጫወተው ቦሌ ክ/ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ላይ በርካታ ተጫዋቾችን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ በመስጠቱ እንዳለፉት ዓመታት ከወገብ በላይ ሆኖ ማጠናቀቅ ባይችልም በሜዳ ላይ ወጥ የሆነ ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ በማሳየት ውድድራቸውን በ26 ጨዋታዎች በሰበሰቧቸው 28 ነጥቦች አስረኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ማጠናቀቅም ችለዋል።
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ውስጥ ከሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች መካከል አንዱ በሆነው አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ አራቱን የውድድር ዘመናት እየሰለጠነ የሚገኘው ቡድኑ በአሰልጣኙ ስር በሊጉ ከሚያደርጉት ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ባሻገር ለተከታታይ አራት ዓመታት የሊጉን የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ጠራርጎ በመውሰድ በብቸኝነት “የፀባይ ቻምፒዮን” እንድንላቸው ሆኗል። በተደጋጋሚ ይህንን የፀባይ ዋንጫ በየዓመቱ እንዴት ማምጣት እንደተቻለ የቡድኑ አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ ሲናገር “በጨዋታው ሜዳ ውስጥ በጨዋታው በበለጠ ለተጋጣሚ ቡድን ክብር እንሰጣለን ጨዋታን ተጫዋቾቼ በሚጫወቱበት ሰዓት ፌር በሆነ መልኩ ሰውን የመጉዳት ፣ የመጣል ከጥፋቶች ጋር በተያያዙ ከዳኞች ጋር ጭቅጭቅ እና በአጉል ጥፋቶችም ካርድን እንዳይመለከቱ እንደ ቡድን ሰርተናል” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን “ለዳኞች ለተጫዋቾች ለደጋፊዎች የሚኖረን ክብር እንደ ቡድን የተሰራ እና የታወቀ ነው ከዛ በተረፈ የምንጫወትበት መንገድ ጥሩ እና ማራኪ ስለሆነ በፌር ፕለይ እስከ አሁን እየተሸለምን ያለነው ለዚህ ነው።” ሲሉ አሰልጣኙ ለዝግጅት ክፍላችን ጠቁመዋል።