ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ መቐለ 70 እንደርታ

መቐለ 70 እንደርታዎች ላለመውረድ እያደረጉት በሚገኘው ፍልሚያ ላይ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ መውረዱን ካረጋገጠው ወልዋሎ በወንጂ ሁለገብ ስታዲየም ይፋለማሉ።

በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ብርቱ ፉክክር ከሚደረግባቸው ተጠባቂ የደርቢ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው ወልዋሎ እና መቐለ 70 እንደርታ የሚያገናኘው ጨዋታ ቢጫዎቹ ለክብር ምዓም አናብስት ደሞ ላለመውረድ በሚያደርጉት ፉክክር ተስፋ የሚያሰጣቸውን ድል ለማግኘት በወንጂ ሁለገብ ስታዲየም ይፋለማሉ።

መውረዳቸውን ካረጋገጡበት ወቅት ጀምሮ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ሆነ በመንፈስ ረገድ የተሻሻለ ብቃት በማሳየት ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች በተለይም ባለፉት ስምንት የጨዋታ ሳምንታት በብዙ ረገድ የጎለበተ እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል። በአመዛኙ ወጣት ተጫዋቾች ባሰለፉባቸው በቅርቡ የተከናወኑ መርሐግብሮች በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ የተሻሻለ ብቃት ያሳዩት ቢጫዎቹ በመጨረሻው ጨዋታ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ግብ ተቆጥሮባቸው ሽንፈት ቢያስተናግዱም በመርሐግብሩ ጨምሮ ከድሬዳዋ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አርባምንጭ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ በተለይም በመከላከሉ ረገድ ጠንካሮች ነበሩ። በነገው ዕለትም በቅርብ ሳምንታት የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት የጨመረው መቐለ እንደመግጠማቸው የኋላ ክፍላቸውን ጥንካሬ ማስቀጠል የሚኖርባቸው ሲሆን በፊት መስመር ላይ የሚስተዋልባቸው የአፈፃፀም ድክመትም መቅረፍ ይኖርባቸዋል።

በመጥፎው የወልዋሎ የውድድር ዓመት ላይ አዎንታዊ ጎኖች እንጥቀስ ከተባለ የቡድኑ የወጣት ተጫዋቾች አጠቃቀም ሳያነሱ ማለፍ ንፉግነት ነው፤ ቡድኑ ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋናው ሊግ መውረዱ ቢያረጋገጥም እንደነ ናትናኤል ኪዳነ፣ ሱልጣን በርሐ፣ ናሆም ኃይለማርያም፣ ዳዊት ገብሩ እና ሚክኤለ ኪዳነ የመሳሰሉ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች ለሊጉ አስተዋውቋል።

በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ላለመውረድ እያደረጉት በሚገኘው ፍልሚያ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ነገ ያደርጋሉ።

በመሪው መድን ከገጠማቸው የአንድ ለባዶ ሽንፈት በኋላ እጅ ያልሰጡት ምዓም አናብስት ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሁለት ድሎች እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ማስመዝገብ ችለዋል። አሁን ላይ በወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ባለፉት መርሐግብሮች ራሱን ከሽንፈት ቢያርቅም ነጥብ በተጋራባቸው ጨዋታዎች ላይ ካሳየው ብቃት አንጻር የጣላቸው ውድ ነጥቦች ለቡድኑ አስቆጪ ነበሩ። ቡድኑ ከዚህ ቀደም ዋነኛ ችግሩ የነበረው የመከላከል ድክመት መቅረፍ መቻሉ እንዲሁም በጨዋታዎች ላይ የሚፈጥራቸው ዕድሎች በጥራትም ሆነ በቁጥር ማሳደግ ቢችልም የማባከን አባዜውን ማስተካከል ይኖርበታል። ቡድኑ በተለይም ጠንካራ ቡድኖች በገጠመባቸው ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ላይ በመልካም ጎኑ የሚጠቀስለት ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጉ እንደ አወንታ ማንሳት የሚቻል ቢሆንም በማቀበል እና ወደ ግብ በመሞከር ውሳኔ ላይ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የሚታይባቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ድክመት መቅረፍ ቀዳሚ ሥራው መሆን ይገባዋል።

በወልዋሎ በኩል ኤፍሬም ኃይለማርያም እና ሳምሶን ተካ በጉዳት፤ ሳምሶን ጥላሁን እና ሰመረ ኪዳነ ማርያም ደግሞ በህመም ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ የሀብታሙ ንጉሴ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው እንዲሁም ዳዋ ሆቴሳ በቤተሰብ ችግር ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። መቐለ 70 እንደርታዎች ጉዳት ላይ ከሰነበተው መናፍ ዐወል ውጭ ከቅጣትም ሆነ ጉዳት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ 5 ጊዜ ተገናኝተው 2 ጊዜ አቻ ሲለያዩ መቐለ 2፣ ወልዋሎ 1 ጊዜ ድል አስመዝግበዋል። ምዓም አናብስት 4፣ ቢጫዎቹ ደግሞ 2 ጎል አስቆጥረዋል። (በመቐለ 70 እንደርታ አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ አልተካተተም)።