ፈረሰኞቹ የውጪ ተጫዋች እንዳያመጡ እግድ ላይ ቢሆኑም ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ሊቀላቅሉ እንደሆነ ታውቋል።

በ1928 የተመሰረተው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አሠልጣኝ፣ ቴክኒክ ዳይሬክተር እንዲሁም ተጫዋቾች ትውውር መርሐ ግብር እያወከናወነ የሚገኝ ሲሆን የቡድኑ አዲስ አሠልጣኝ ሚቾ ቡድናቸውን እያዋቀሩ ያሉበትን መንገድ በፕረዘንቴሽን ገለፃ ሲያደርጉ እንዲሁም የቡድን አባላቶቻቸውን ሲያስተዋውቁ ሁለት የውጪ ተጫዋቾች በዝርዝራቸው ውስጥ እንዳለ ተስተውሏል።
በፊፋ የውጪ ተጫዋች እንዳያስፈርም በዚህ የዝውውር መስኮት የታገደው ክለቡ በምን አግባብ የውጪ ተጫዋቾችን እያመጣ እንደሆነ ከስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሀን አባላት ጥያቄ ቀርቦ አሠልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት አሠልጣኝ ሚቾ “ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን ያመጣነው ባህሉን የአየር ሁኔታውን እና ክለቡን ቀድመው እንዲለምዱ ነው።
“አንደኛው ተጫዋች ለምሳሌ ወደ ፈረንሳይ ሊሄድ ነበር ፤ ግን ጊዮርጊስ መምጣት የመረጠው ለተጫዋችነት ህይወቱ ትልቅ አበርክቶ ስላለው ነው። ተጫዋቾቹ ሰኞ ኢትዮጵያ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የህክምና ምርመራ አድርገው የቡድኑን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ከመጀመሪያ ጀምሮ ይቀላቀላሉ።” ብለዋል።
የውጪ ተጫዋቾቹ ሰኞ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ቡድኑን ቢቀላቀሉም እግዱ ሳይነሳ ይፋ ተመዝግበው ጨዋታ እንደማያደርጉ ቢጠነቅም የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ቶፊቅ እየመጡ ያሉት ተጫዋቾች ከኦክቶበር 19 በኋላ መፈረም እና መጫወት እንደሚችሉ አመላክተው ከዛ በፊት ግን ከሰኞ ጀምሮ ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምዳቸውን እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።
በተያያዘ ከአሚን ነስሩ ውጪ ሁሉም ቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ከ25 ዓመት በታች እንደሆኑ ተመላክቷል።

