አንጋፋውን ክለብ ከ23 ዓመታት ጥበቃ በኋላ ከዋንጫ ጋር ያስታረቁ ተጫዋቾች በተናጠል ሲዳሰሱ…!
የ2017 ውድድር ዓመት በመድን አሸናፊነት ተጠናቋል፤ ሁሉም ቡድኖች ካመጡት ስንቅ አቅምሰውናል። ከክፍያ ስርዓት ጋር በተያያዙ፣ ከአቅም በታች በመጫወት ተጠርጥረዋል በተባሉ አካላት እንዲሁም በአሳዛኝ እና አሳማኝ ሽንፈቶች ታጅቦ የተጠናቀቀው ዓመት ብዙ የጠረጴዛ ዙርያ ውይይቶች የሚያስፈልጉት ቢሆንም ለዛሬ አንጋፋው ኢትዮጵያ መድን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለ ክብር እንዲሆን ካስቻሉ አባላቶች ውስጥ ከ400 ደቂቃ በላይ ቡድናቸውን ያገለገሉትን በተናጠል ለመዳሰስ የቻምፒዮኖቹን ቤት እንጎብኝ።
አቡበከር ኑራ
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ለቡድናቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ካደረጉ ግብ ጠባቂዎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ቁመታሙ በሊጉ በእያንዳንዱ ደቂቃ ላይ የተሳተፈ ብቸኛው ግብ ጠባቂ ነው። በሊጉ ጥቂት ግቦች ባስተናገደው የመከላከል ጥምረት ቁልፍ ሚና የነበረው አቡበከር በዓመቱ በ 22 ጨዋታዎች መረቡን በማስከበር እንዲሁም ጥቂት በማይባሉ መርሐግብሮች ላይ ቡድኑ በጨዋታ እንዲቆይ ያስቻሉ ወሳኝ ኳሶች ያዳነ ሲሆን በተጨማሪም በውድድር ዓመቱ 1 ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቷል። በዚህ መሰረት ባሳየው ወጥ የሆነ ብቃት እና በሜዳ ላይ በነበረው አገልግሎት በሻምፒዮኖቹ ቤት ቁልፍ አባል ከመሆን አልፎ የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ ክብር መጎናፀፍ በትክክል እንደሚገባው ምስክር አያሻውም።
ንጋቱ ገብረሥላሴ
የቡድን ተጫዋች፣ በተሰጠው የስራ መደብ ተግቶ በመስራት የማይታማ እንዲሁም ወጥነት ንጋቱ ገብረስላሴን የሚገልፁ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከፍተኛ አካላዊ ፍልሚያ በሚደረግበት ቦታ ላይ ከጉዳት ነፃ ሆኖ እንዲሁም ለካርድ ተጋላጭ በሆነ የሜዳ ክፍል ላይ እየተሰለፈ በውድድር ዓመቱ 3 የቢጫ ካርዶች ብቻ በመመልከት ከጉዳትና ቅጣት ነፃ ሆኖ ከሳምንት ሳምንት ቡድኑን ያገለገለው ተጫዋቹ ካሳየው ብቃት በተጨማሪ ያበረከተው የማያቋርጥ አገልግሎት የኋላ ክፍሉ ወሳኝ ሰው ያስብለዋል።
ከዚህ ቀደም በተከላካይ አማካይነት ቦታ ሲጫወት የምናውቀው ንጋቱ በ34 ጨዋታዎች በወጥነት ከማገልገሉ በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያቶች የተከላካይ ክፍሉ በሳሳበት ወቅት ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ተጣምሮ ከሁሉም የሰመረ ጥምረት አድርጎ የመድን የመከላከል ጥንካሬ ያስቀጠለ የቡድኑ የኋላ ክፍል ምሰሶ ነው። ኢትዮጵያ መድን በውድድር ዓመቱ በ34 ጨዋታዎች ውስጥ በ22ቱ መረቡን እንዲያስከብር እና 15 ግቦች በማስተናገድ በሊጉ ዝቅተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ ቡድን እንዲሆን ካስቻሉ የመከላከል አደረጃጀቱ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሁለገቡ ተጫዋች ያበረከተው አስተዋፅኦ ከቁልፍ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ያስችለዋል።
በረከት ካሌብ
በውድድር ዓመቱ ለሊጉ አዲስ ግኝት ከነበሩ ወጣት ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ በረከት ካሌብ ነው።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከዚህ የተሻለ ምርጥ
የወጣት ተጫዋች ዝውውር ነበር ለማለት ያዳግታል። የበረከት ብቃት፣ ወጥነት እና ትጋት ለእግር ኳስ ቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌንም ጭምር ‘Surprise’ ያደረገ ነበር ማለት ይቻላል። በመጀመርያው የሊጉ ቆይታው ላይ ብዙዎች የሀገራችን ወጣት ተጫዋች ያልታደሉት ወጥነት ያለው ብቃት ያሳየው የቀኝ መስመር ተከላካዩ በዓመቱ በ29 ጨዋታዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለ ሲሆን በተለይም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች መከላከል ላይ የነበረው ብቃት ቡድኑ በሊጉ ጥቂት ግቦች ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እንዲኖረው አስተዋፅኦ አድርጓል።
ረመዳን የሱፍ
ረመዳንን ሁሉም የሚያውቀው በግራ መስመር ተከላካይነቱ ነው፤ መከላከል እና ማጥቃት በሚዛናዊነት ማስኬድም ጥርሱን የነቀለበት ሞያው ነው። ከዚህ ቀደም በግራ መስመር ተከላካይነት ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሁለት የሊግ ክብሮች ያነሳው እና ዘንድሮ ሦስተኛ የሊግ ዋንጫውን ያሳካው እንዲሁም በዋናው ቡድን ደረጃ በ2011 አጋማሽ በቢጫና አረንጓዴ የስሑል ሽረ ማልያ ከሊጉ ጋር የተዋወቀው ተጫዋቹ ዘንድሮ ግን የመስመር አጥቂ ሆኖ መጫወት እንደሚችል እና ወሳኝ ግቦች የማስቆጠር አቅም እንዳለው አስመስክሯል። በውድድር ዓመቱ በ25 ጨዋታዎች ተሰልፎ 7 ግቦች ማስቆጠር የቻለው ረመዳን ከጉዳት ጋር እየታገለ ከቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሐመድ አበራ እና አቡበከር ሳኒ ቀጥሎ በርከት ያሉ ግቦች ያስቆጠረ መሆኑ ሲታይ አስተዋፅኦው የማይተካ ነበር ለማለት ያስደፍራል።
ሀይደር ሸረፋ
ድል ባለበት ሁሉ የማይጠፋው ሀይደር ሸረፋ በእግር ኳስ ሕይወቱ አራተኛ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ሦስተኛ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫው ከፍ አድርጓል።
መድን እስከ 8ኛው ሳምንት ድረስ የቡድኑ ማገር የነበረው ጋቶች ፓኖም ካጣ በኋላ በአዲስ ሚና ቡድኑን ለማገልገል የተገደደው ሀይደር ሽግሽጉ በአቋሙ እክል እንዳልፈጠረበት እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ድረስ በተካሄዱ ወሳኝ መርሐግብሮች አስመስክሯል። በዓመቱ በ 33 ጨዋታዎች የተሳተፈው ተጫዋቹ ወገኔ ገዛኸኝ እና ዳዊት ተፈራ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ከኋላ ቆሞ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሏል።
አንድ አምበል በርካታ ቁልፍ የአመራር ባህሪያትን ማካተት ግድ ይለዋል። መሪነት፣ ጥሩ ተግባቦት፣ አብነታዊ መሆን እና ቡድኑን የማነሳሳት ክህሎት ደግሞ ወሳኝ ናቸው። በተጠቀሱት መለኪያዎች ስንመዝነው ሀይደር ሸረፋ የተሟላ መሪ ነው ማለት እንገደዳለን። ወሳኝ በነበሩ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎች ያሳየው መሪነት እና ብቃት ደግሞ የዚህ ምስክሮች ናቸው።
መሐመድ አበራ
በቀጣይ ዓመታት ከሊጉ ምርጥ አጥቂዎች መደብ ሊያሰልፈው የሚችል እምቅ አቅም እንዳለው ባስመሰከረበት ዓመት ቡድኑን ለዋንጫ ክብር ያበቁ አስር ግቦች ያስቆጠረው ወጣቱ መሐመድ አበራ የእግር ኳስ ሕይወቱ ምርጥ ዓመት ላይ የሻምፒዮኖቹ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን በቡድኑ አጨዋወት ላይ የማይተካ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች ይጠቀሳል። ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ የተጫወተው አጥቂው በእግር ኳስ ሕይወቱ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባሳካበት ዓመት ላይ በቡድኑ የማጥቃት ክፍል ላይ ቁልፍ ሚና የነበረው ሲሆን ዕድሎች መፍጠር እና ወሳኝ ግቦች ማስቆጠርም የእርሱ ዋነኛ የስራ ድርሻዎች ነበሩ።
ዳዊት ተፈራ
በኢትዮጵያ መድን የዘንድሮ ስኬት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ከነበራቸው ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ የሚጠቀሰው አማካዩ ዳዊት ተፈራ በውድድር ዓመቱ ለቡድኑ ያላቸውን ጨምቀው ወጥ የሆነ ግልጋሎት ከሰጡ የቡድኑ አባላት አንዱ ነው። በውድድር ዓመቱ በሰላሣ አራቱም የጨዋታ ሳምንታት ተሳትፎ አራት ግቦች ያስቆጠረው አማካዩ በተለይም በ17ኛው ሳምንት ላይ ሀድያ ሆሳዕና ላይ ያስቆጠራት ብቸኛ የማሸነፍያ ግብ ወሳኝ ነበረች። ከዚህ ቀደም በሲዳማ ቡና ሦስት በቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሁለት የውድድር ዓመታት በማሳለፍ አንድ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው አማካዩ የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በእግር ኳስ ሕይወቱ በርከት ያሉ ጨዋታዎች ያደረገበት ሲሆን ከአገልግሎቱም በተጨማሪ በጨዋታዎች የነበረው አበርክቶም ከቡድኑ ወሳኝ አባላት አንዱ ያደርገዋል።
ወገኔ ገዛኸኝ
በውሃ ሰማያዊ እና ነጭ ለባሾች ቤት ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ተሰላፊዎች አንዱ ወገኔ ነው፤ የተጫዋቹ አበርክቶ በቁጥሮች ብቻ አስደግፎ መግለፅም ንፉግነት ነው። የግብ ዕድሎች መፍጠር፤ ከቆሙ ኳሶችም ሆነ ከክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ የሆኑ ኳሶች በማመቻችት በቡድኑ የዋንጫ ጉዞ ወሳኝ ሚና የነበረው ተጫዋቹ በመድን የማጥቃት አጨዋወት ውስጥ አይተኬ ሚና ከነበራቸው ተሰላፊዎች አንዱ ነው።
በውድድር ዓመቱ በሰላሣ አራት ጨዋታዎች በመሰለፍ በቡድኑ በርከት ያሉ ደቂቃዎች ካገለገሉ ሦስት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ወገኔ በዓመቱ አምስት ግቦች ያስቆጠረ ሲሆን በተለይም አራት ግቦች ባስቆጠረባቸው የመጨረሻዎቹ አምስት ሳምንታት ጥሩ ብቃት በማሳየት ዓመቱን አጠናቋል።
በፕሪምየር ሊግ የሦስት ዓመት ቆይታው በ86 ጨዋታዎች ተሳትፎ 15 ግቦች ከመረብ ጋር ያዋሃደው ወጣቱ አማካይ ከዓመት ዓመት ራሱን እያሻሻለ እዚህ ደርሷል፤ በቀጣይም ከሀገሪቱ ምርጥ አማካዮች አንዱ የመሆን አቅም እንዳለው መናገርም የቃሉ ግነት እምብዛም ነው።
አቡበከር ሳኒ
በዘንድሮ የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት አሳይተው ግን ብዙም ካልተወራላቸው ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አቡበከር ሳኒ በእግር ኳስ ሕይወቱ ምርጡን የውድድር ዓመት አሳልፏል። በዘንድሮ የውድድር ዓመት ስምንት ግቦች በማስቆጠር በቡድኑ የዋንጫ ጉዞ ጉልህ አስተዋፅኦ የነበረው ተጫዋቹ በሊጉ በ32 ጨዋታዎች የተሳተፈ ሲሆን ይህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልቂጤ ከተማ ቆይታው በአንድ የውድድር ዓመት ከተሳተፈባቸው ጨዋታዎች ቁጥር የሚልቅ ነው። አቡበከር በአሳዳጊ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአምስት ዓመታት የዋናው ቡድን ቆይታው የሊጉን ዋንጫ ማሳካት ቢችልም አበርክቶው ግን ጥሩ እንቅስቃሴና መልካም አበርክቶ ካደረገበት የዘንድሮው የውድድር ዓመት የሚነፃፀር አይደለም። ያስቆጠራቸው ግቦች፣ በወሳኝ ጨዋታዎች ባሳየው እንቅስቃሴ እንዲሁም ከቅጣት እና ጉዳት ነፃ ሆኖ በወጥነት ማገልገሉም በቡድኑ የዋንጫ ጉዞ ወሳኝ ከነበሩ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ያስችለዋል።
ያሬድ ካሳየ
ወጣት ነው ዘመኑን የዋጀ፤ ቦታው የሚፈልገውን ነገር ያሟላ ግን በውድድር ዓመቱ የመድን ስኬት ላይ ስሙ ሲነሳ እምብዛም አይስተዋልም ተስፈኛው ያሬድ ካሳየ!
በውድድር ዓመቱ በ29 ጨዋታዎች የተሳተፈው ያሬድ በገብረመድኅን ኃይሌ ቡድን ላይ የነበረው አበርክቶ አይተኬ ነበር። ጉዳት ካስተናገደበት የውድድር ዓመቱ ጅማሮ ውጭ የአሰልጣኙ ቀዳሚ ተመራጭ የነበረው ወጣቱ በመከላከሉ ላይ ብቻም ሳይሆን በተጋጣሚ ሜዳ ላይም እየተሳተፈ በማጥቃቱ ላይ እርዳታ መለገስ መለያዎቹ ነበሩ።
በቀጣይ ዓመታት በቦታው ከሚጠቀሱ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ የመሆን አቅም ያለው ተጫዋቹ በሜዳ ላይ የነበረው አበርክቶ እንዲሁም የሰጠው የማያቋርጥ ግልጋሎት ከመድን ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ ያደርገዋል።
ዋንጫ ቱት
ኢትዮጵያ መድኖች አምበላቸውን ሚሊዮን ሰለሞን ባጡበት ወቅት ለቦታው መተማመኛ ከሆኗቸው የመሃል ተከላካዮች ውስጥ ወጣቱ ዋንጫ ቱት አንዱ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በሁለተኛው ዓመቱ የሊጉን ክብር ያሳካው ወጣቱ ተጫዋች በውድድር ዓመቱ በ15 ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈ ሲሆን በተለይም ዘጠኝ ጨዋታዎች በተሰለፈበት ሁለተኛው ዙር ጥሩ አበርክቶ አድርጓል። አሰልጣኝ ገብረመድኅን ሀይሌ የመሰለፍ ዕድል ከሰጡት በኋላ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሱን እያሻሻለ የሚገኘው ታዳጊው በዓመቱ ሁለት ቀይ ካርዶች የተመለከተ ሲሆን ለካርድ ያለው ተጋላጭነት መቀነስም በቀጣይ የሚጠበቅበት ስራ ነው።
አዲስ ተስፋየ
ላለፉት አስር ዓመታት በፕሪምየር ሊጉ የመጫወት ልምድ ያለው የመሃል ተከላካዩ አዲስ ተስፋየ በውድድር ዓመቱ በ12 ጨዋታዎች የተሳተፈ ሲሆን በተለይም ቡድኑ ወሳኝ የመሀል ተሰላፊው ሚሊዮን ሰለሞንን ባጣበት ሁለተኛው ዙር ላይ ከዋንጫ ቱት ጋር እየተፈራረቀ በቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ ላይ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። የተሻለ የመሰለፍ ዕድል ባገኘበት ሁለተኛው መንፈቅ ላይ በስምንት ጨዋታዎች የተሳተፈው የመሃል ተከላካዩ ዘንድሮ ከመድን ጋር ያሳካው የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫም የመጀመርያው ነው።
ምንተስኖት አዳነ
የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ፍሬ የሆነው ምንተስኖት አዳነ በውድድር ዓመቱ በ21 ጨዋታዎች ተሳትፎ 492 ደቂቃዎች ቡድኑን ማገልገል የቻለ ሲሆን በውድድር ዓመቱ በሜዳ ላይ ከነበረው አበርክቶ በበለጠ ልምዱ በዋንጫው ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው የቡድኑ አባላት የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
አለን ካይዋ
ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ሻሸመኔ ከተማን ለቅቆ መድንን ከተቀላቀለ በኋላ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ጥሩ መሻሻል እንዲያስመዘግብ አስተዋጽኦ ካደረጉ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ዩጋንዳዊው አለን ካይዋ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ከተሳተፉ 49 የውጭ ተጫዋቾች ውስጥ የሊጉን ዋንጫ ያሳካ ብቸኛው ተጫዋች ነው። በውድድር ዓመቱ በ23 ጨዋታዎች የተሳተፈው አጥቂው በሊጉ አምስት ግቦች ያስቆጠረ ሲሆን በተለይም ከረዥም ጊዜያት በኋላ በቋሚነት ከጀመረበት የ21ኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ወሳኝ በነበሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ፋሲል ከነማ ጋር በተደረጉ ጨዋታዎች ወሳኝ ግቦች አስቆጥሯል።
አብዲሳ ጀማል
ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ አራት ዓመታት ያሳለፈበትን አዳማ ከተማ ለቅቆ ኢትዮጵያ መድንን የተቀላቀለው አብዲሳ ጀማል ከጉዳት ጋር እየታገለ ባሳለፈው የውድድር ዓመት በአስራ ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈ ሲሆን በዓመቱ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ጉዳት እስከ አስተናገደበት የሰባተኛው ሳምንት ጨዋታ ድረስ የቡድኑ ቋሚ ተሰላፊ የነበረው እና በመርሐግብሮቹ ሁለት ግቦች በማስቆጠር አንድ ግብ የሆነ ኳስ ያመቻቸው አጥቂው በጉዳት ምክንያት ጥሩ አጀማመሩን ማስቀጠል ባይችልም በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ጥሩ አበርክቶ አድርጓል።
ሚሊዮን ሰለሞን
በሁለተኛው የውድድር ዓመቱ መንፈቅ ላይ ባልታወቀ ምክንያት ከቡድኑ ጋር ያልነበረው ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ምንም እንኳን በወሳኙ የውድድር ወቅት ላይ ክለቡን ባያገለግልም በመጀመርያው ዙር ከቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ እንደነበር አይካድም። በውድድር ዓመቱ በ12 ጨዋታዎች ተሰልፎ 2 ግቦች ያስቆጠረው ተከላካዩ ቡድኑ በዋንጫ ፉክክሩ መሰረት እንዲይዝ በማስቻልም ጥሩ አበርክቶ አድርጓል።