አሜሪካ ተጓዡ ቡድን ውስጥ አንድ አዲስ ተጫዋች ተቀላቅሏል

አሜሪካ ተጓዡ ቡድን ውስጥ አንድ አዲስ ተጫዋች ተቀላቅሏል

ከስብስቡ ውጪ በሆኑ ተጫዋቾች ምትክ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾች እንደተተኩ ቢነገርም አንድ ሌላ አዲስ ተጫዋች አሁን ቡድኑን መቀላቀሉን አውቀናል።

በቀጣይ ሳምንት ቅዳሜ በዩናይትድ ስቴትስ ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ጨዋታ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባ ዝግጅት በማድረግ ከጀመረ አራተኛ ቀኑ ሆኗል። ጥሪ የተደረገላቸው 23 ተጫዋቾች ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም ከቪዛ ፍቃደ አለማግኘት እና የቪዛ ጊዜያቸው በማለቁ አስር ተጫዋቾች ከስብስቡ ውጪ መሆናቸውን እና በምትኩ አምስት ለአዳዲስ ተጫዋቾች ጥሪ መደረጉን ትናንት ምሽት ዘግበን ነበር።

አሁን ደግሞ ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘነው መረጃ ስድስተኛ ተጫዋች ሆኖ አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ቡድኑን መቀላቀሉን አውቀናል። ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምድ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን አጥቂው ዳዋ ሆቴሳም ከቡድኑ ጋር አብሮ ልምምድ እየሰራ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ ዜና ጥሪ ከተደረገላቸው አዳዲስ ተጫዋቾች መካከል ሻይዱ ሙስጠፋ ብቻ ቡድኑን ተቀላቅሎ ልምምድ ሲሰራ አንተነህ ተፈራ፣ አማኑኤል ኤርቦ፣ ሱሌይማን ሀሚድ ካሉበት ከተማ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ሲሆን ዛሬ ሆቴል ገብተው ነገ ልምምድ እንደሚጀምሩ አረጋግጠናል። ከነዓን ማርክነህ ግን በግሉ ለሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት ልምምድ በአሜሪካ የሚገኝ በመሆኑ እንደ ሱራፌል ዳኛቸው እዛው ቡድኑን የሚቀላቀል ይሆናል።