👉 “የኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ ኢንዱስትሪ እንደሆነ የሚያሳይ ክፍያ ነው።” አቶ ክፍሌ ሰይፈ
በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከፍተኛው የሆነው የገንዘብ ክፍፍል ይፋ መሆኑን ተከትሎ እና ሌሎች ጥያቄዎችን አስመልክቶ ከአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ጋር ቆይታ አድርገናል።
2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከብሮድካስት እና ስም ስያሜ መብት የሚያገኙት ክፍፍል ይፋ ሆኗል። በዓመቱ ክለቦቹ የሚደርሳቸው ክፍፍል በአፍሪካ በከፍተኛነቱ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሆኖ በተመላከተው በዚህ ክፍፍል ዙርያ እና በሌሎች ተዛማች ጥያቄዎች አካተን ከአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋር ሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጋለች።
የገንዘቡ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ምክንያቱ ምን እንደሆነ መጀመርያ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ነው የተፃፈው። እንዲህ ያለ ክፍያ ተከፋፍሎ አያውቅም። ክፍያውን ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጥፍ ያሳደገው የውጭ ምንዛሪው ፤ የዶላር መጨመር ነው። አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ወደ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱ ያመጣው ነው። ይህ የኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ ኢንዱስትሪ እንደሆነ የሚያሳይ ክፍያ ነው።”
የክፍያ ስርዓቱ መመርያ ጣሱ በሚባሉ ክለቦች ላይ የሚደረገው በማጣራት ሳያልቅ ክፍያው ድልድል መውጣቱ ምርመራው በመቋረጡ? ወይስ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ ሥራ አስኪያጁ ሲመልሱ “ማጣራቱ ይቀጥላል ሆኖም በደረጃ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም። ማጣራቱ ተደርጎ መክፈል ካለባቸው ይከፍላሉ አለበለዚያ አይወዳደሩም ምክንያቱም ውድድር ላይ አይደሉም። ስለዚህ ደረጃ ላይ ተፅዕኖ አይመጣም። ተፅዕኖ ካመጣ የሚቀጥለው ዓመት ነው። ይህም በዚህ ዓመት ምርመራ ተጫዋቹ የክፍያ ሥርዓቱን ከጣሰ እና ክፍያውን አልከፍል ካለ ከውድድር ሊታገድ ይችላል እንጂ የደረጃ ለውጥ አያመጣም። ክለቦችም መመርያውን ቢተላለፉ በተመሳሳይ ይሆናል እንጂ ደረጃ ለውጥ አይኖረውም በማለት ገልፀዋል።”
የትግራይ ሦስት ክለቦች ክፍያ አለማግኘት ምክንያት ምን እንደሆነ ስንጠይቃቸው በጠቅላላ ጉባዔው በተወሰነው መሠረት ወደ ውድድር ሲገቡ በልዩ ሁኔታ በመሆኑ እና የአክስዮን ማኅበሩ አባል ባለመሆናቸው ክፍያ ውስጥ አለመካተታቸውን ገልፀዋል።”