ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ባህርዳር ከተማ ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ባህርዳር ከተማ ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ባህርዳር ከተማ ተጨማሪ አራት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ሲቀላቅል የሁለት ነባሮችን ውል ደግሞ አራዝሟል።

በ2018 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት እስከ አሁን ሦስት አዳዲስ እና ሦስት ነባሮችን ፊርማ ያገኘው ባህርዳር ከተማ አሁን ደግሞ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሁለት ነባሮችን ውል ደግሞ ለተጨማሪ አመት አራዝሟል።

አማካዩዋ ሳራ ኪዶ ለሁለት ጊዜያት ያህል ተመልሳ ከተጫወተችበት ሀዋሳ ከተማ ወደ ባህርዳር ተጉዛለች። ከአርባምንጭ ከተማ የጀመረው የእግር ኳስ ህይወቷ በሀዋሳ እና መቻል ካሳለፈች በኋላ ቀጣዩዋ መዳረሻዋ የጊዮን ንግስቶቹ ቤት ሆኗል።

ሌላኛዋ ፈራሚ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከተገኘች በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ይርጋጨፌ ቡና ፣ አዳማ ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በድሬዳዋ ያሳለፈችው የመሐል ተከላካዩዋ ደመቀች ዳልጋ ሆናለች። በአማካይ ስፍራ በልደታ ክፍለ ከተማ ፣ ሱሉልታ እና ድሬዳዋ ከተማ የተጫወተችው ማናአየሽ ተስፋዬ ፣ በሀዋሳ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ በግብ ጠባቂነት ያገለገለችው ገነት ኤርሚያስ አራተኛዋ በድምሩ ደግሞ የቡድኑ ሰባተኛዋ ፈራሚ ተጫዋች መሆን ችላለች።

ከአዳዲሶቹ በተጨማሪ የአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱው ቡድን የአማካዮቹን ቅድስት ገነነ እና ወርቅነሽ መሠለን ውል ለተጨማሪ ዓመት ውላቸውን አድሷል።