ሙሉጌታ ምሕረት ወደ ሌላ ክለብ ማምራቱን ተከትሎ አፋጣኝ ስብሰባ ማምሻውን የተቀመጠው የሀዋሳ ከተማ ቦርድ አዲሱን አሰልጣኝ መምረጡን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከምስረታው አንስቶ እየተካፈሉ ከሚገኙ ሁለት ቡድኖች መሐል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሦስት አሰልጣኞት ሲመራ የቆየ ሲሆን በተለይ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረትን የኋላ ኋላ ከቀጠረ በኋላ ከወራጅ ቅርቃር ተላቆ በአስደናቂ ጉዞ በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጡ ይታወሳል። ለቀጣዩ የ2018 የውድድር ዘመን በሙሉጌታ ምሕረት እየተመራ እንደሚቀጥል ሲጠበቅ የነበረው ቡድኑ በትናንትናው ዕለት አሰልጣኙ ወደ መቻል ማምራቱን ተከትሎ የክለቡ ቦርድ በዛሬው ዕለት ማምሻውን ባደረገው ፈጣን ስብሰባው አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ምርጫውን ማድረጉን በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች።
የሀዋሳን ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኖችን በማሰልጠን የክለብ ህይወትን የጀመረው አሰልጣኝ ተመስገን በተለያዩ ጊዜያቶችም የኢትዮጵያን ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖችን ጭምር በማሰልጠን ጥሩ ጊዜያቶችን ማሳለፍም ችሏል። 2011 የሀዋሳ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ በመቀጠል በከፍተኛ ሊጉ ደቡብ ፓሊስን በፕሪምየር ሊጉ ወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡናን ያሰለጠነው አሰልጣኙ በአሁኑ ሰዓት የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ረዳት በመሆን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ሲያገለግል ቆይቶ በመጨረሻም ወደ ቀደመው ቤቱ በአንድ ዓመት ውል በይፋ ተቀላቅሏል።