የራምኬል ጀምስ ማረፊያ የት ይሆን?

የራምኬል ጀምስ ማረፊያ የት ይሆን?

የመሐል ተከላካዩ ራምኬል ጀምስን ለማስፈረም ሁለት ክለቦች ተፋጠዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሊጉ ጠንካራ ተከላካይ መሆኑን እያሳየ የሚገኘው እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡደን ተመራጭ የሆነው የኋላ ደጀኑ ራምኬል ጀምስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለው የውል ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣይ ማረፊያ የት የሆናል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ተጫዋቹም በአሜሪካ የነበረውን የሙከራ ጊዜ አገባዶ ከመጣ በኋላ የቀጣይ ዓመት ቆይታውን ለመወሰን ከጫፍ ደርሷል።

ሶከር ኢትዮጵያም ለጉዳዮ ቅርበት ካላቸው ምንጮቿ እንዳረጋገጠችው ከሆነ ራምኬል በአብዛኛውን ነገሮች ከሀዋሳ ከተማ ጋር የተስማማ ሲሆን በትናትናው ዕለትም የሜዲካል ምርመራ አድርጎ በመጨረስ ዝውውሩን በፊርማ ያጠናቅቃል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ሆኖም ኢትዮጵያ ቡና ትናንት ማምሻውን የክለቡ ቦርድ ተጫዋቹ ወደ ሚገኝበት ቦታ በመሄድ ራምኬልን ከሀዋሳ ከተማ ለመጥለፍ ተጫዋቹን ለማግባባት ንግግር አድርገው በቀጠሮ ተለያይተዋል። በዚህም መሰረት ዛሬ ከደቂቃዎች በኋላ ሜክሲኮ ወደ ሚገኘው የክለቡ ፅህፈት ቤት ራምኬል በመሄድ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ዙርያ ድርድር በማድረግ አንበላቸውን ለማስቀረት ብናማዎቹ እንደሚሰሩ ሰምተናል።

አሁን የሚጠበቀው ራምኬል አስቀድሞ በውስጥ ስምምነት ላደረገው ለሀዋሳ ከነማ ይፈርማውን ያኖራል ወይስ ለሦስት ዓመት ለቆየበት ኢትዮጵያ ቡና ፊርማውን ያኖራል የሚለው ውሳኔው የተጫዋቹ መሆኑን አውቀናል።