የሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ ምድብ ድልድል ይፋ ሆነ

የሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ ምድብ ድልድል ይፋ ሆነ

በሴካፋ ካጋሜ ካፕ ኢትዮጵያን ወክሎ እንደሚሳተፍ የሚጠበቀው ኢትዮጵያን ቡና ምድቡን አውቋል።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ቀደም ብሎ 12 ቡድኖች በሚሳተፉበት የካጋሜ ዋንጫ የሚሳተፉ ቡድኖች ማሳወቁ ይታወቃል ዛሬ ደግሞ የምድብ ድልድሉ ይፋ ሆናል። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ቡና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በካፍ ኮንፌደሬሽን ካፕ ከገጠመው ኬንያ ፖሊስ፣ ጋርዴ ኮትስ እና ሲንጋዳ ብላክ ስታርስ ጋር በምድብ አንድ ተደልድሏል።

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ከቀናት በፊት በይፋዊ ‘የፌስቡክ’ ገፁ በውድድሩ እንዲሳተፍ ጥሪ እንደቀረበለት እና የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ በቅርቡ በሚያደርገው ስብሰባ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ከመግለፁ ውጭ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ በይፋ አልገለፀም።

የሴካፋ አባል ሀገራት ክለቦች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ከነሐሴ 27 እስከ መስከረም 5 በታንዛኒያ ዳሬሰላም የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ጨምሮ አል ሂላል ኦምዱርማን፣ ኤ ፒ ኣር ፣ ቫይፐርስ፣ ሲንጋዳ ብላክ ስታርስ፣ ኬንያ ፖሊስ፣ ፍላምቤው ዱ ሴንተር፣ ጋርዴ ኮትስ፣ አል አሃሊ፣ ኤል ሜሪክ ቤንቲዩ እና ምላንዴግ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።