በዝውውር ገበያው ምንም ዓይነት ተሳትፎ ሳያደርግ የቆየው አዳማ ከተማ የግብ ዘብ ለማስፈረም ተቃርቧል።
አሰልጣኝ ስዩም ከበደን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው አዳማ ከተማ ለቀጣይ ዓመት ቡድኑን ለማጠናከር አሰልጣኝ ከሾመ ወዲህ ወደ ዝውውሩ ለመግባት ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ለቀናት ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል። ሆኖም ዘግይቶም ቢሆን የግብ ዘቡን አላዛር ማርቆስን ለማስፈረም ተቃርቧል።
የግብ ዘቡ አላዛር ማርቆስ በሀዋሳ ከተማ ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ከዘለቀ በኋላ በጅማ አባ ጅፋር እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በአንድ ወቅት የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ፣ በ2014 የዓመቱ ተስፈኛ ተጫዋች ሆኖ ተመርጦ እንደነበረ ሲታወቅ አሁን መዳረሻው አዳማ ከተማ ሆኗል።
በቀጣዮቹ ቀናት አዳማ በስፋት ወደ ዝውውር መስኮቱ በመግባት ጠንከር ያሉ ዝውውሮችን እንደሚፈፅም ለክለቡ ቅርበት ካላቸው ምንጮቻችን መረጃዎችን አግኝተናል።