ወልዋሎ ዩጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል።
በዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በማስፈረም እና የነባሮችን ውል በማራዘም ስብስባቸውን አጠናክረው ቀደም ብለው በአዳማ ከተማ እና በመቀመጫ ከተማቸው ዓዲግራት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በማከናወን በድሬ ካፕ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ዩጋንዳዊውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።
ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማው ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩጋንዳው ቡል ቆይታ የነበረው ጆኤል ሙታኩብዋ ነው። ባለፈው ዓመት የጂንጃው ክለብ ቆይታው ባደረጋቸው 29 ጨዋታዎች ውስጥ በ14ቱ መረቡን ሳያስደፍር የወጣው እና በዓመቱ በዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ በርከት ያሉ ደቂቃዎች ሜዳ በመቆየት ቀዳሚ የሆነው ግብ ጠባቂው በ2025 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሩ ዩጋንዳን ወክሎም በስድስት ጨዋታዎች በቋሚነት ተሰልፏል።
ከዚህ ቀደም በሀገሩ ክለቦች ክየቱሜ፣ ኤክስፕረስ እንዲሁም ኢንቴቤ መጫወት የቻለው ተጫዋቹ
ከቡል ጋር ያለውን ውል መጠናቀቁን ተከትሎ በሀገሩ ክለብ ‘Kcca’ በጥብቅ ሲፈለግ ቢቆይም ወደ ወልዋሎ ለመቀላቀል መስማማቱን ተከትሎ በዛሬ ዕለት ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን በነገው ዕለት የሕክምና ምርመራውን አጠናቆ በይፋ ፊርማውን ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል።