የሉሲዎቹ አለቃ ዮሰፍ ገብረወልድ ከነገውን ወሳኝ ፍልሚያ በፊት አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
በታንዛንያ በተካሄደው የመጀመርያ ጨዋታ የሁለት ለባዶ ሽንፈት አስተናግደው ኢትዮጵያን ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ አህጉራዊ መድረክ ለመመለስ የመጨረሻ ዘጠና ደቂቃ የሚቀራቸው የሉሲዎቹ አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ውጤቱን ለመቀልበስ ምን ዓይነት ዝግጅት አድርጋችኋል ?
“የነበረን የዝግጅት ጊዜ አጭር ቢሆንም ከታንዛንያ ጋር ያደረግነውን የጨዋታ ‘ቪድዮ’ በመመልከት የነበሩንን ደካማ እና ጥሩ ጎኖች በመለየት በነበሩን ውስን ቀናት ውስጥ በዛ ላይ የተመሰረተ ዝግጅት አድርገናል። ከፈጣሪ በታች እኔም ሆነ ተጫዋቾቼ የምንችለውን በማድረግ ውጤቱን ለመቀልበስ በጥሩ መነሳሳት ላይ እንገኛለን።”

የሎዛ አበራ መኖር ቡድኑን ምን ያክል ያግዛል ?
“በታንዛንያው ጨዋታ ላይ ያገኘናቸውን የግብ ዕድሎች ወደ ግብነት አለመቀየራችን ዋጋ አስከፍሎናል። አሁን ግን የሎዛ አበራ መኖር ካላት ልምድ እና ችሎታ ጋር ተደምሮ ውጤቱን ለመቀየር በደንብ ያግዘናል።”

በመጨረሻም “የድሬደዋ ህዝብ እግር ኳስ ወዳድ፣ ለእግርኳስ ፍቅር ያለው እንደሆነ ይታወቃል። ስለሆነም የማስተላለፈው መልዕክት የሀገር ጉዳይ ነው መጥተው እንዲያበረታቱን እጠይቃለው ብለዋል”።


