በሙከራዎች የታጀበ እጅግ ማራኪ ፉክክር በተደረገባቸው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ7ኛው ሳምንት የምድብ አንድ የ2ኛ ቀን ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና መሪነቱን ሲያጠናክር ፋሲል ከነማ ወደ ሊጉ አናት ተጠግቷል።
መቻል ከ ሲዳማ ቡና
በሰንጠረዡ አናት የተቀመጡ ቡድኖች ያገናኘው እና ተጠባቂ የነበረው ጨዋታ ግብ ያስተናገደው ገና በመጀመርያው ደቂቃ ነበር፤ ኮሊን ኮፊ ከእጅ ውርወራ የተላከችለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ገፍቶ ያስቆጠራት ግብም ጦሩን መሪ ማድረግ ችላለች። ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ በጀመረው ማራኪ ጨዋታ መቻሎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠርም ተቃርበው ነበር፤ አማኑኤል ዮሐንስ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ተመቶ ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ ተጠቅሞ መቶት ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል ሲመልሰው ኮሊን ኮፊ የተመለሰው ኳስ በድጋሚ ሞክሮት ወደ ውጭ የወጣው ኳስም የጦሩን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበ ሙከራ ነበር።

ከቀዝቃዛው አጀማመር አገግመው በርከት ያሉ ዕድሎች መፍጠር የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ሬድዋን ናስር ከቆመ ኳስ አሻግሮት ያሬድ ባየ በግንባሩ ገጭቶት አልዮንዜ ናፍያን በጥሩ ቅልጥፍና ባወጣው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በ19ኛው ደቂቃም በብሌስ ናጎ ግሩም ሙከራ ካደረጉ በኋላ በመቻል ሳጥን የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት በያሬድ ባየህ አማካኝነት በማስቆጠር አቻ መሆን ችለዋል። ከግቦቹ መቆጠር በኋላ መቻሎች በረከት ደስታ በመልሶ ማጥቃት ሳጥን የደረሰውን ኳስ አግኝቶ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ባዳነው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ
ያሬድ ባየህ በሁለት አጋጣሚዎች ከመዓዝን የተሻሙ ኳሶች ተጠቅሞ በግንባር ባደረጋቸው ሙከራዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።

በብርቱ ፉክክር እና ጥሩ እንቅስቃሴ የቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር።
ኢሞሮ ማናፍ መሬት ለመሬት ባደረጋት ዒላማዋን የጠበቀች ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት መቻሎች ቸርነት ጉግሳ ወደ ሳጥን አሻግሯት በረከት ደስታ ከግቡ አፋፍ ሆኖ መቷት ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል የመለሳት አስቆጪ ሙከራ እንዲሁም ፈቱዲን ጀማል አክርሮ መቷት ኮከብ ሆኖ የዋለው ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል የመለሳት ኳስም ጦሩን መሪ ለማድረግ ተቃርበው ነበር። በአጋማሹ ብርሃኑ በቀለ በግንባር ባደረጋት እንዲሁም ብለስ ናጎ ከግቡ አፋፍ ሆኖ ባመከናት ወርቃማ ሙከራ ዕድሎች የፈጠሩት ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት የአሸናፊነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ሬድዋን ናስር ከቆመ ኳስ አሻግሯት ያሬድ ባየህ በግንባር ያስቆጠራት ግብም ለሲዳማ ቡና ሦስት ነጥብ ያስገኘች ግብ ነች።
በሁሉም መመዘኛዎች ድንቅ ፉክክር የተደረገበት፤ በሙከራዎች እና በሁሉም የሜዳ ክፍሎች በተደረጉ አካላዊ ፍልሚያዎች የታጀበው እንዲሁም 11 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች እና 37 ጥፋቶች በተፈፀሙበት ጨዋታም ሲዳማ ቡና በያሬድ ባየህ ሁለት ግቦች ታግዞ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በሰንጠረዡ አናት የተቀመጡ ክለቦች ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር በመጀመርያው አጋማሽ የፋሲል ከነማዎች ብልጫ የታየበት ነበር። በሁሉም ረገድ የተሻሉ በነበሩት ዐፄዎቹ በኩል
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በጨዋታው ጅማሮ ላይ በረዥሙ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ሳጥን ገፍቶ በመምታት ባደረገው ወርቃማ ዕድል እንዲሁም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ቃልኪዳን ዘላለም በግንባሩ ገጭቶ አግዳሚው በመለሰበት ሙከራ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።
ብሩክ አማኑኤል ከመዓዝን በቀጥታ ያደረጋት እንዲሁም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በአግባቡ ካበረደ በኋላ ያልተጠቀመባት ዕድልም ሌሎች በዐፄዎቹ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። ጌታነህ ከበደ ከመስመር አሻግሯት ቢኒያም በላይ ያልተጠቀመባት ዕድል እና ተባረክ ሄፋሞ በሞየስ ፖውቲ ስህተት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራም በሐይቆቹ በኩል ይጠቀሳሉ።

ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ የሀዋሳ ከተማ ብልጫ የታየበት ሲሆን ጌታነህ ከበደ በሁለት አጋጣሚዎች ከርቀት ያደረጋቸው ሙከራዎች እንዲሁም ተቀይሮ የገባው የአብሥራ ደግፌ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ያገኘው ኳስ መቶ ግብ ጠባቂው በድንቅ መንገድ ያወጣበት ሙከራም ቡድኑን ለማድረግ ተቃርበው ነበር። በብዙ ረገድ ተሻሽለው የተመለሱት ሐይቆቹ ከተጠቀሱት ሙከራዎች በኋላም ብሩክ ታደለ ከግራ መስመር አሻግሯት የአብሥራ ደግፌ ባመከናት እጅግ አስቆጪ ሙከራ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቀዝ ብለው የታዩት ዐፄዎቹ በአቤኔዘር ዮሐንስ አማካኝነት ካደረጉት ለግብ የቀረበ ሙከራ በኋላ በ77ኛው ደቂቃ መሪ የምታደርጋቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ቃልኪዳን ዘላለም ከምኞት ደበበ አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ሳጥን ይዟት የገባውን ኳስ ተጠቅሞ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ያዋሃዳት ግብም ዐፄዎቹን መሪ ያደረገች ኳስ ነች። ሐይቆቹ ከግቧ በኋላ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም የዐፄዎቹን ተከላካዮች አልፈው ሙከራዎች ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቋል።


