የ8ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ
አራት ድሎች እና ሦስት ሽንፈቶች በማስተናገድ በሊጉ ነጥብ ያልተጋራው ብቸኛው ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአስራ ሁለት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ መድንን ካሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው ሁለት የሊግ እና አንድ የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገደው ክለቡ ወደ ድል ጎዳና ለመመለስ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነውን የፊት መስመሩ ማስተካከል ይኖርበታል።
በሊጉ ድል ማድረግ ካልቻሉ ሁለት ክለቦች አንዱ የሆነው አርባምንጭ ከተማ አራት አቻዎች እና ሦስት ሽንፈቶች አስመዝግቦ በአራት ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሀድያ ሆሳዕናን በገጠመበት የመጨረሻው ጨዋታ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ተቃርቦ የነበረው ቡድኑ በጎዶሎ ተጫዋች ከጨረሳቸው ሦስት ጨዋታዎች አንፃር ውስን መነቃቃት የታየበት ቢሆንም አሁንም ሁለንታዊ መሻሻልን ይሻል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ20 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተፋለሙ ሲሆን በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ 2 ጊዜ ድል አድርጎ የተቀሩት 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዲሱ አቱላ ለዛሬው ጨዋታ ብቁ ነው፤ ሆኖም ሻይዱ ሙስጠፋ፣ አሚን ነስሩ እና ፉዐድ አብደላ ግን አሁንም በጉዳይ ምክንያት በጨዋታው አይሳተፉም። በአርባምንጭ ከተማ በኩል በርናንድ ኦቼንግ እና አንዱአለም አስናቀ አሁንም በጉዳት ጨዋታዎች ያመልጧቸዋል። አካሉ አትሞ ግን ከአንድ ጨዋታ ቅጣት በኋላ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።
መቻል ከ ድሬዳዋ ከተማ
ሦስት ሦስት የድልና የአቻ ውጤቶች እንዲሁም አንድ ሽንፈት በማስመዝገብ በአስራ ሁለት ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች መሪውን እግር በእግር ለመከታተል በዛሬው ጨዋታ ድል ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ድንቅ ፉክክር በተደረገበት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ያሳየው ብቃት በአወንታ የሚጠቀስለት ቢሆንም የቆሙ ኳሶች መከላከል ላይ ያለውን ድክመት መቅረፍ ይጠበቅበታል።
በእስር ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻው ሳምንት ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባል። በሽረ ምድረ ገነት ሽንፈት በቀመሱበት ጨዋታ ላይ በብዙ ረገድ የተዳከመ የፊት መስመር የነበራቸው ብርቱካናማዎቹ ከሁሉም ነገር በላይ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
መቻል በዛሬው ጨዋታ የመሐመድ አበራ እና ብሩክ ማርቆስን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም፤ ድሬዳዋ ከተማዎች ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።
በሊጉ ከዚህ ቀደም ሀያ አራት ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መቻሎች በአስራ ሁለት አጋጣሚ ማሸነፍ ሲችሉ በአንፃሩ ድሬዳዎች ደግሞ ሦስት ጨዋታዎች እንዲሁም የተቀሩት ዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።
ነገሌ አርሲ ከ ሸገር ከተማ
ሁለት ድል፣ ሦስት አቻ እና ሁለት ሽንፈት አስመዝግበው በዘጠኝ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነገሌ አርሲዎች ሦስተኛው ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበው ደረጃቸው ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ወደ ሀዋሳ ካቀና በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎችን ያሳካው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ከሽንፈት ከመራቁም በተጨማሪ እንቅስቃሴው ላይ መሻሻሎች ታይተዋል።
በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ ሦስቱም የውጤት ዓይነቶች በማስመዝገብ ስምንት ነጥብ የሰበሰቡት ሸገር ከተማዎች ከዛሬው ተጋጣምያቸው አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው 13ኛ ላይ ተቀምጠዋል። ከአራት ሽንፈት አልባ ሳምንታት በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገባው ቡድኑ በቀዳሚነት የግብ ማስቆጠር ችግሩን መፍታት ይኖርበታል። ቡድኑ በሊጉ አራት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ከዚህ ውስጥ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የተገኙት ሁለቱን ብቻ ናቸው።
በሸገር ከተማ በኩል ገዛኸኝ ደሳለኝ በጨዋታው የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ሌሎች የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በነገሌ አርሲ በኩል አብዱልባሲጥ ከማል፣ በረከት ወልዴ እና ኢብሳ በፍቃዱ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም።
ሁለቱም አዲስ አዳጊ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።


