በሀዋሳ የተመቸውና በድል አድራጊዎች ጎዳና የተንጎማለለው ክስተቱ የሰጎኖቹ ስብስብ…
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በየዓመቱ ከሚደጋገሙ ክስተቶች አንዱ አዲስ አዳጊዎች በመጀመርያው ዓመታቸው የሚገጥማቸው ፈተና አንዱ ነው። በርግጥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በመጀመርያ ዓመታቸው የሊጉን ዋንጫ ያሳኩ እንደ ጅማ አባጅፋር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ጥሩ ተፎካካሪ በመሆን ደግሞ ኢትዮጵያ መድን፣ ፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም አብዛኞቹ አዲስ አዳጊ ቡድኖች ግን በውጤት ቀውስ እና ላለመውረድ በሚደረግ ትግል ውስጥ ሲዳክሩ ማየት የተለመደ ነው።
ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀሉ ሸገር ከተማ እና ነገሌ አርሲ ግን ከወዲሁ ከተለመደው ፈተና ፈቀቅ ብለው ዓመቱን ጀምረውታል። በርግጥ ሊጉ ገና በጅማሮ ላይ ነው፤ ቀሪ 29 የጨዋታ ሳምንታት እየቀሩ ስለ አንድ ቡድን የውድድር ዓመት ጉዞ ለመተንበይ አዳጋች ነው። ሆኖም ሁለቱ ክለቦች ባለፉት ዓመታት ሊጉን ከተቀላቀሉ ቡድኖች አንፃር ሲታይ አጀማመራቸው በብዙ ረገድ የተሻለና ተስፋ ሰጪ ነው። ለዛሬ ደግሞ ውድድሩ ወደ ውቢቷ ሀዋሳ ካመራ በኋላ የተመቸው ነገሌ አርሲን እንቃኛለን!
ሰገኖቹ ከሌሎች የሊጉ ክለቦች አንፃር ሲታይ ወደ ዝውውር ዘግይተው ነበር የተቀላቀሉት። የመጀመርያው የዝውውር መስኮቱ ፈራሚያቸው ዳዊት ተፈራን ያገኙበት ዕለትም ነሐሴ 28 ሲሆን ወቅቱም አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ዝውውሮቻቸውን ለማገባደድ የተቃረቡበት ጊዜ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የሰገኖቹ የዝውውር ተሳትፎ ባለፉት ዓመታት ወደ ሊጉ ያደጉ ክለቦች በመጀመርያው የዝውውር መስኮት ከነበራቸውን አካሄድ አንፃር ሲታይ በተወሰነ መልኩ የተለየ ነበር ማለት ይቻላል። ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደጉ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ይዞ ከመቀጠሉም በዘለለ በቋሚነት እየተጠቀመ በመዝለቅ ብዙዎች ያልደፈሩት አካሄድ ተክትሏል። ሆኖም ቡድኑ በዝውውር መስኮቱ የነበረው ተሳትፎ እንዲሁም ያለው የቡድኑ ጥራት እና ጥልቀት ካስመዘገበው ውጤት ጋር ሲታይ አስደናቂ ነው።
ሰጎኖቹ በመጀመርያዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈቶች እና ሦስት የአቻ ውጤቶች አስመዝገበው ነበር ዓመቱን የጀመሩት። በመለያ ምት ሀድያ ሆሳዕናን ካሸነፉበት የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ ውጭም በሊጉ ድል ሳያደርጉ ነበር አዲስ አበባን የተሰናበቱት። በውቢቷ ሀዋሳ የነበራቸው በድሎች እና በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች ፌሽታ የታጀበ ጊዜ ግን እጅግ ድንቅ ነበር።

አሰልጣኝ ቱሉ ደስታ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በአንድ የድሕረ ጨዋታ ቡድናቸው በደጋፊው ፊት በሀዋሳ ተሻሽሎ እንደሚቀርብ በገለፁበት ወቅት ቡድኑ መጠነኛ መሻሻል ያሳይ ይሆናል። ከሚሉ መላ ምቶች በዘለለ በዚ ደረጃ በውጤት ጎዳና ይጎማለላል ብሎ የገመተ አልነበረም። ሆኖም
በሀዋሳ ባደረጓቸው 4 ጨዋታዎች 3 ድሎች እና 1 የአቻ ውጤት ከማስመዝገባቸው በተጨማሪ በቡድኑ የታየው ሁለንተናዊ መሻሻል አስደናቂ ነው። ማግኘት ከሚገባቸው 12 ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ጥለው 10 ነጥቦች ማሳካታቸውም ቡድኑ በሀዋሳ ምን ዓይነት አስደናቂ ጊዜ እንዳሳለፈ ምስክሮች ናቸው።
በርግጥ የቡድኑ አጀማመር ቀዝቃዛ የሚባል ቢሆንም ከአምስተኛ ሳምንት በኋላ ያሳየው ፈጣን መሻሻል ግን ትኩረትን ይስባል። በተለይም በተጠቀሱት ጨዋታዎች የነበራቸው እንቅስቃሴ እና በቡድኑ የታየው ድንቅ የድል ረሀብ የሕዳር ወር የሊጉ አዝናኝ እና ሳቢ ቡድን የሚል ክብር ያጎናፅፋቸዋል። ከመመራት ተነስተው ጠንካራውን አዳማ ከተማ ባሸነፉበት መርሐ-ግብር እና ከሁለት ለባዶ መመራት አገግመው ከሸገር ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ግቦች ነጥብ ማሳካታቸው እንዲሁም የወቅቱ የሊግ ቻምፕዮን መድን ባሸነፉበት ጨዋታ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎም የብዙዎች ትኩረት የሳበ ነበር።
ወጣቱ አሰልጣኝ ቱሉ ደስታ በ5ኛው ሳምንት በ3 ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ተቀምጠው የነበሩት ሰገኖቹ ላሳዩት ድንቅ መሻሻልም የአምበሳውን ድርሻ ይወስዳል። አሰልጣኙ በሊጉ ከፍተኛው ነጥብ ባስመዘገቡባቸውና ጠንካራ ቡድኖች በገጠሙባቸው አራት ሳምንታት የነበራቸው ጥሩ ጨዋታ አመራር እና የውሳኔ አሰጣጥ ብቃትም አስደናቂ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨምሮ በመጨረዎቹ 5 ጨዋታዎች 4 ግቦች ያስቆጠረው ወጣቱ የመሀል ተከላካይ ሮሆቦት ሶላሎ እንዲሁም ተስፈኛው የፊት መስመር ተጫዋች ካቤ ብዙነህ ለቡድኑ ውጤት ማማር ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ ነው። በጥምረት ደረጃም በመጀመርያዎቹ 5 ጨዋታዎች 2 ግቦች ብቻ ካስቆጠረ በኋላ በመጨረሻዎቹ 4 ጨዋታዎች በጥሩ ጎን ከሚጠቀስ መሻሻል ጋር 7 ግቦችን ያስቆጠረው የፊት መስመር ይጠቀሳል።
ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደገ እና በመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎው የሚገኘው ወጣቱ አሰልጣኝ ቱሉ ደስታ በቀጣይ በመጨረሻዎቹ 4 መርሐ-ግብሮች በጨዋታ በአማካይ 1 ግብ ያስተናገደውን የተከላካይ ክፍል ማሻሻል እንዲሁም በቡድኑ የተስተዋለው ዕድገት እና ተነሳሽነት በማስቀጠል በያዙት የውጤታማነት መንገድ የመዝለቅ ትልቅ ኃላፊነት ይጠቃቸዋል።


