አዳማ ከተማ ዝውውሩን በይፋ ተቀላቅሏል

አዳማ ከተማ ዝውውሩን በይፋ ተቀላቅሏል

አዳማ ከተማ ሁለት አዲስ ፈራሚዎችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

በዝውውር መስኮቱ በይፋ መሳተፍ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ስብስባቸውን የሚያጠናክሩ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል። የመጀመሪያው ፈራሚ የተከላካይ አማካዩ ይሁን እንደሻው ሲሆን ቀደም ሲል በመተሃራ ስኳር ፋብሪካ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ሀዲያ ሆሳዕና ፣ ፋሲል ከነማ እና አርባምንጭ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈ እንዲሁም በ2010 ከጅማ አባ ጅፋር እና 2013 ከፋሲል ከነማ ጋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ሁለት ጊዜ ማሳት የቻለ ባለ ብዙ ልምድ ተጫዋች ነው።

ሁለተኛው ክለቡን የተቀላቀለው ፈራሚ ደግሞ የመስመር አጥቂው ቦና ዓሊ ነው። የእግር ኳስ ጅማሬውን በአምቦ አካዳሚ ያደረገው ቦና በፕሪሚየር ሊጉ ለጅማ አባ ጅፋር፣ ለአዳማ ከተማ እንዲሁም ላለፉት ሁለት ዓመታት ለመቐለ 70 እንደርታ መጫወት የቻለ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ቀድሞ ቡድኑ አዳማ ከተማ በድጋሚ ተመልሷል።