የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር የነበረው ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኘው ማራኪ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
በአሳቴዩ ስታዲየም ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ባገናኘው እጅግ ሳቢ እና ለተመልካች ማራኪ በነበረው ጨዋታ 5ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ፈድሪክ ኑሲ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክርም በግቡ አግዳሚ ለጥቂት ወጥቶበታል። ጥሩ የኳስ ፍሰቶችን ባስመለከተን ጨዋታ 27ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ኳስ ከቅጣት ምት ከተመስገን በጅሮንድ የተሻማውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባር ገጭቶ ወደ ራሱ ግብ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው አጋማሽ የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመፈተሽ የጨዋታ ብልጫ ማሳየት ቢችልም በመጨረሻው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ በታየ የተጫዋቾች ግለኝነት እና ለግብ ከመጠን በላይ መቸኮል ምክንያት ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ሳይጠቀምበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ ተሽለው የቀረቡ ሲሆን በአንጻሩ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ጥንቃቄ የተሞላበት መከላከልን ምርጫቸው አድርገዋል። ሲዳማዎች በመከላከል ላይ ተመስርተው በረጃጅም ኳሶች አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ለማድረግ ቢሞክሩም ለረጅም ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ግልጽ የሆነ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ቆይቷል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ግን እንቅስቃሴው ተቀይሮ በ84ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ጉልላት ከሻይዱ ሙስጠፋ ጋር ያደረጉት ድንቅ የአንድ-ሁለት ቅብብል ለግብ የቀረበ ሙከራ ቢያስገኝም ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል አድኖታል። ይሁን እንጂ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ጉልላት ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ያስቆጠረው እጅግ ግሩም ግብ ለቡድኑ ነፍስ የዘራ ሲሆን ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።


