ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የሚካሄዱ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ነጌሌ አርሲ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

ሰጎኖቹ እና ቢጫዎቹ የሚያደርጉት የሳምንቱ የመጀመሪያ መርሐግብር 07፡00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።

ከ6 ጨዋታዎች በኋላ በፋሲል ከነማ ሽንፈትን የቀመሱት ነጌሌዎች ብርቱ ፉክክር ባደረጉበት ጨዋታ በተለይም የከቤ ብዙነህ ጠንካራ ሙከራዎች ወደ ጎልነት ተቀይረው ነጥብ ይዘው አለመውጣታቸው ቁጭት እንደሚጭርባቸው ቢታመንም የተከላካይ መስመር ስህተቶች ግን በዚህ ሳምንትም ጎልተው ታይተዋል። በሀዋሳ ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው ቡድኑ ለጨዋታ መንገዱ የአዲስአበባ ስታዲየም የተመቸው አይመስልም። የተከላካዮች ወደኋላ የሚደረጉ ቅብብሎች ትልቅ ስጋት መሆናቸው በድጋሚ ወደ ስታዲየሙ ሲመለሱ እየታዩባቸው በመሆኑ ይህንን ማስተካከል የአሰልጣኝ ቱሉ ደስታ የቤት ሥራ ነው።

ከፍተኛ መሻሻል እያሳዩ የሚገኙት በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የሚመሩት ወልዋሎዎች ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ሰብስበዋል። መቐለ እና ንግድ ባንክን አሸንፈው ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1ለ1 ተለያይተው ነጥብ የተጋሩት ቢጫዎቹ በራስ መተማመናቸው ከፍ እያለ ይገኛል። ሆኖም በዛሬው ጨዋታ ከተለያዩ አማራጮች የግብ ዕድል የሚፈጥረውን የሰጎኖችን ስብስብ ለመመከት ብርቱ ፍልሚያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ወልዋሎዎች በዛሬው ጨዋታ ተከላካዩ ነጻነት ገብረመድኅንን በቅጣት አማካዩ ኤፍሬም ኃይለማርያምን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ይህ ጨዋታ ለሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ግንኙነት ነው።

 

አርባምንጭ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

 

የደረጃው ግርጌ ላይ ተከታትለው የተቀመጡ ቡድኖች የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማሳካት ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።

በውጤት ማጣት ምክኒያት ሙሉ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን አሰናብቶ በጊዜያዊነት የዋልያዎቹን የቀድሞ ኮከብ አበባው ቡጣቆ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት የሾሙት አዞዎቹ ከ10 ጨዋታዎች አምስት ተሸንፈው አምስት አቻ በመለያየት በ5 ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን 12 ጎሎችን ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ማስተካከል የጊዜያዊ አሰልጣኙ የመጀመሪያ የቤት ሥራ ይሆናል።

እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ አሰልጣኛቸውን ጌታቸው ዳዊትን አሰናብተው አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን የሾሙት መቐለዎች በኢትዮጵያ ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜው ቢሸጋገሩም በፕሪሚየር ሊጉ ግን በ4 ነጥቦች የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በማጥቃት እንቅስቃሴው የማይታማው ቡድኑ ውጤት ማስጠበቅ ላይ ያለበት ከፍተኛ ክፍተት ለዚህ ቀውስ የዳረገው ሲሆን አዲሱ አሰልጣኝ ይህን ለመቅረፍ ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል አንዱዓለም አስናቀ ከገዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን በርናንድ ኦቼንግ ጉዳቱ ለረጅም ጊዜ የሚያቆየው በመሆኑ ወደ ሀገሩ መመለሱን አረጋግጠናል። እንዲሁም አማኑኤል ጎበና በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። መቐለ 70 እንደርታዎች በዛሬው ጨዋታ ሱሌይማን ሐሚድ፣ ዘርኢሰናይ ብርሃነ እና ዮሐንስ ዓፈራ በጉዳት ተመስገን ተስፋዬን ደግሞ በቅጣት አያሰልፉም። ሕመም ላይ የነበረው ተከላካዩ ጊት ጋትኮች ግን አገግሞ ልምምድ ጀምሯል ሆኖም በጨዋታው የመሳተፉ ነገር አጠራጣሪ ነው።

ቡድኖቹ በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ምዓም አናብስት ሁለት ጊዜ ድል ሲያደርጉ በ2 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱ መቐለ 7 ግቦች ሲያስቆጥር አርባምንጭ 2 ግቦች አስቆጥሯል።

ባህር ዳር ከተማ ፋሲል ከነማ

የጣና ሞገዶቹ እና ዐፄዎቹ የሚያደርጉት የደርቢነት መንፈስ ያለው ጨዋታ 10፡00 ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።

ባልተለመደ ሁኔታ ስጋቶች የበዙባቸው የጣና ሞገዶቹ ባለፉት ዓመታት የነበረው ከፍተኛ በራስ መተማመናቸው አሁን አብሮ አይገኝም። በቦዲቲ ከተማ ከኢትዮጵያ ዋንጫ ውጪ የሆነው በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ከ10 ጨዋታዎች ሦስት አሸንፎ በሦስቱ ተሸንፎ በአራቱ አቻ በመለያየት በ13 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ውጤቶቹን ቶሎ ካልሰበሰበ ካለው የቡድን ስብስብ ጥበት አንጻር ረጅም የሆነው ሊግ ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል። በዛሬው ጨዋታም ተጋጣሚያቸው 3 ጎሎች ብቻ የተቆጠሩበት የመከላከል አደረጃጀት እንደመያዙ የሚጠብቃቸው ፉክክር ከፍ ያለ ነው።

እጅግ ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ በሊጉ 3 ጎሎች ብቻ ተቆጥሮበት ከሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማ ከሰሞኑ አነጋጋሪ በነበረው የቡድኑ ዋና ቁልፍ ተጫዋች ምኞት ደበበ በቀይ ካርድ መውጣት እና 4 ጨዋታ መቀጣት ምክንያት በመከላከሉ ረገድ አንዳች ነገር እንዳያጣ ተሰግቷል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳኅሌ የገነቡት በማራኪ ጨዋታ ውጤታማ የሆነ ቡድን ዛሬ ይህንን ጨዋታ አሸንፎ ሲዳማ ቡና እስኪጫወት የሊጉ መሪ ለመሆን ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅበታል።

በባህር ዳር ከተማ በኩል ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ክንዱ ባየልኝ ውጪ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ በፋሲል ከነማ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት ሀብታሙ ተከስተ እና ኪሩቤል ዳኘ ከጉዳት አገግመው ሲመለሱ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ብሩክ አማኑኤል በጉዳት እንዲሁም ቃልኪዳን ዘላለም እና ምኞት ደበበ በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 12 ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 8 ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ሲፈፅሙ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ ባለድል መሆን ችለዋል። በጨዋታዎቹ ዐፄዎቹ 9 ግቦች እንዲሁም የጣና ሞገዶቹ ደግሞ 6 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

 

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ

 

ከመመራት ተነስተው ድል ተቀዳጅተው የመጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ 12፡00 ሲል በአ.ሳ.ቴ.ዩ ይደረጋል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች መልስ መቐለን ከመመራት ተነስተው 2ለ1 ያሸነፉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህ ውጤት ተነሳስተው ለዛሬው  ጨዋታ በራስ መተማመናቸው እንደሚጨምር ይጠበቃል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሁሉም ጎሎችን ያስተናገደው የመከላከል ሽግግራቸውን ማስተካከል ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ ቢሆንም የቡድኑ ዋና አጥቂ ብሩክ በየነ በጉዳት አለመኖሩ የአጥቂ መስመራቸው ላይ ክፍተት እንዳይፈጥር አሰልጣኝ ካሊድ መሐመድ የሚመርጡት የጨዋታ መንገድ ይጠበቃል።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ ከአራት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፈው በሁለቱ አቻ የተለያዩት የጦና ንቦቹ ሸገር ከተማን ከመመራት ተነስተው 3ለ1 ያሸነፉ ሲሆን አሰልጣኙ መሳይ ተፈሪም የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል። ቡድኑ በሊጉ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች በሁሉም ጎሎች የተቆጠሩበት ሲሆን ይህንን ማስተካከል ለነገ የማይባል ሥራቸው ነው። በዛሬው ዕለትም የተጋጣሚን ፈጣኑ አጥቂ ተመስገን ብርሃኑን መቆጣጠር ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የግብ ጠባቂው ኦውሱ አንድሪውስ መሰለፍ በመጠኑ አጠራጣሪ ሲሆን በባለፈው ጨዋታ የትከሻ ጉዳት ያስተናገደው ብሩክ በየነ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ አይኖርም። በአንጻሩ ጉዳት ላይ የነበረው ተከላካዩ ዳግም ንጉሤ አገግሞ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በወላይታ ድቻ በኩል ካርሎስ ዳምጠው ብቻ በጉዳት ምክንያት አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ12 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን እኩል 5 5 ጊዜ ተሸናንፈው የተቀሩ ሁለት መርሐግብሮች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።