የኢትዮጵያ ቡና ዋና አሠልጣኝ አብይ ካሣሁን ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል።
የአንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮ የውድድር ዓመት በ11 ጨዋታዎች 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ይታወቃል። በርከት ያሉ የቡድኑ ደጋፊዎች በቡድኑ አሁናዊ ውጤት ደስተኛ ባለመሆን ከፍ ያሉ የተቃውሞ ድምፆችን ሲያሙ የነበረ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ሲሆን ክለቡም ከቀናት በፊት ለአሠልጣኙ እና ለተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ኢትዮጵያ ቡናን በዋና አሠልጣኝነት እንዲመሩ ሹመት ያገኙት አሠልጣኝ አብይ ካሣሁን እስከ ዓመቱ መጨረሻ በክለቡ የሚያቆያቸው ውል ቢኖራቸውም ከሰዓታት በፊት ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት በይፋ ደብዳቤ ለፅህፈት ቤት ማስገባታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ክለቡም አዲስ አሠልጣኝ ለመሾም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ያወቅን ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት በክለቡ በኩል አዲስ ዜና እንደሚሰማ ይጠበቃል።

