ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ድል ሲቀዳጅ ባንኮቹ እና ነብሮቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ወሳኝ ድል ሲቀዳጅ ባንኮቹ እና ነብሮቹ ነጥብ ተጋርተዋል

በ14ኛ ሳምንት የአ/ሳ/ቴ/ዩ የመጨረሻ የጨዋታ ዕለት 10 ቢጫ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዲያ ሆሳዕና ያለ ግብ ሲለያዩ ኢትዮጵያ መድን ከመመራት ተነስቶ ወላይታ ድቻን አሸንፏል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

በዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ መሪነት በተካሄደው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር ተደርጎበታል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ዓለማየሁ ለነብሮቹ 9ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አዲስ ግደይ ለባንኮቹ ከቅጣት ምት ያደረጓቸው እና ዒላማቸውን ቢጠብቁም ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራዎች የተፈጠሩ የመጀመሪያ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

በግብ ዕድሎች በኩል የተጠበቀውን ያህል ፉክክር ሳይደረግበት በቀጠለው ጨዋታ ንግድ ባንኮች 34ኛው ደቂቃ ላይ በሳይመን ፒተር በግንባር የተገጨ ኳስ ሙከራ ካደረጉ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሀዲያዎች ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሱራፌል ጌታቸው ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ብሩክ በየነ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ በጥሩ ብቃት መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በፈጣን ሽግግሮች የግብ ዕድሎችን በተደጋጋሚ መፍጠር ሲችሉ ብሩክ ብፁአምላክ 48ኛ እና 58ኛ ደቂቃ ላይ ካደረጋቸው ሙከራዎች ባሻገር አዲስ ግደይ 52ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ላይ በተሠራ ጥፋት በተሰጠው የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኦውሱ አንድሪውስ ይዞበታል።

ባንኮች 62ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አዲስ ግደይ ከቅጣት ምት ያደረገው ድንቅ ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ጉሽሚያዎች ውጥረቱ እያየለ በሄደበት ጨዋታ ሀዲያዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ በቁጥር ለማነስ ተገድደዋል። አምበሉ ሄኖክ አርፊጮ የባንኩ ሁዘይፋ ሻፊ ላይ በሠራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

የቁጥር ብልጫ ካገኙ በኋላ በተለይም በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ከፍተኛ ብልጫ የወሰዱት ንግድ ባንኮች 90+2ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ጎል ሊያስቆጥሩ እጅግ ተቃርበው አዲስ ግደይ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት ናትናኤል ዳንኤል እና በዛብህ ካቲሶ በተመለሰው ኳስ ያደረጓቸውን ሙከራዎች የሀዲያ ተከላካዮች ተደርበው አግደዋቸዋል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ነጥብ ለመጋራት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ነብሮቹ የጨዋታውን የመጨረሻ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ ናትናኤል ሞገስ 90+8ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ መድን

በዋና ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ መሪነት በተካሄደው እና ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ የጦና ንቦቹ በጨዋታው የመጀመሪያ ዕድል ጎል አስቆጥረዋል። 17ኛ ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ በድንቅ ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ቴዎድሮስ ኃይለማርያም በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮታል።

ዝግ ብለው ወደ ግለት የተመለሱት ኢትዮጵያ መድኖች የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን 35ኛ ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ አለን ካይዋ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በቀላሉ ይዞበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በተመሳሳይ ውጤት የሚጠናቀቅ የነበረ ቢመስልም 43ኛው ደቂቃ ላይ መድኖች የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ያሬድ ካሳየ ከቅጣት ምት ያስጀመረውን ኳስ ዳዊት አውላቸው ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ሞክሮት ቢኒያም ገነቱ ቢመልሰውም የተመለሰውን ኳስ ያገኘው በረከት ካሌብ በግንባር በመግጨት ኳሱን መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተጀመረ 44ኛ ሴኮንድ ላይ መድኖች የፍጹም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ረመዳን የሱፍ በግሩም ክህሎት ተከላካዮችን እያለፈ በነበረበት አጋጣሚ መልካሙ ቦጋለ ከኋላ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ም አለን ካይዋ ግብ ጠባቂውን አቅጣጫ ማሳት ቢችልም የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ እየተደረገበት በማራኪ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ መድኖች 66ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ብሩክ ሙሉጌታ ከረመዳን የሱፍ በተሻገረለት ኳስ ከብሩክ በላቸው ጋር ተቀባብሎ በሳጥኑ የግራ ክፍል እየገፋ በመግባት ካልተጠበቀ አቅጣጫ በድንቅ አጨራረስ ግብ አስቆጥሯል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በሚያገኟቸው ኳሶች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ የቀጠሉት የጦና ንቦች 89ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው በረጅሙ የተሻማውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ከጨረፈው በኋላ ያገኘው ያሬድ ዳርዛ ወደጎን ተገልብጦ ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ሲወጣበት 90+2ኛው ደቂቃ ላይም ከረጅም ሳምንታት በኋላ ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው በረጅሙ ተሻምቶ ንጋቱ ገብረሥላሴ ወደራሱ ሳጥን የጨረፈውን ኳስ አግኝቶት የግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ቢመቻችለትም በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 90+6ኛው ደቂቃ ላይም እንዲሁ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገው ድንቅ ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከዳዊት አውላቸው የ88ኛው ደቂቃ ሙከራ በኋላ ወደ ራሳቸው ሳጥን የተጠጉት ኢትዮጵያ መድኖች መረባቸውን ድጋሚ ሳያስደፍሩ የ2ለ1 መሪነታቸውን አስጠብቀው በጨዋታው እጅግ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።