ባህርዳር ከተማዎች ከ5 ሳምንታት ጥበቃ በኋላ ከድል ጋር እርቅ ሲያወርዱ በተጠባቂው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን 2 ለ 0 ረቷል።

መቻል ከ ባህር ዳር ከተማ
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የታየበት ቢሆንም ዕድሎችን በመፍጠርም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ ግን የጣና ሞገዶቹ ሙሉ ብልጫ ነበራቸው።
በጨዋታው ድንቅ አጀመመር የነበራቸውና የመቻልን የተከላካይ ክፍል የፈተነ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ በሁለቱም የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው ወንድወሰን በለጠ እና ክዋቤና ቦአቲንግ አማካኝነት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ክዋቤና ቧቲንግ ከሳጥኑ ግራ ክፍል አሻግሯት ከግቡ አፋፍ ብቻው የነበረው ወንድወሰን በለጠ በማይታመን መልኩ ወደ ግብነት ያልቀራት ኳስ እንዲሁም በተመሳሳይ መንገድ ወንድወሰን በለጠ ከሳጥኑ ቀኝ ክፍል አሻግሯት ክዋቤና ቧቲንግ ያመከናት ኳስ በጣና ሞገዶቹ በኩል አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ።
ባህርዳር ከተማዎች ከተጠቀሱት አጋጣሚዎችም በተጨማሪ በተጫዋቾች የውሳኔ አሰጣጥ ድክመት ወደ ሙከራነት ያልበቁ ወርቃማ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ መቻሎች ግን በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

መቻሎች ሁለት ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር።
በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ተሻሽለው ለመቅረብ ጥረት ቢያደርጉም ቀድመው መሪ የሆኑበትን ግብ ያስቆጠሩት ግን የጣና ሞገዶች ናቸው። 57ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ከቆመ ኳስ ተሻምታ ወንደሰን በለጠ በግንባሩ ከገጫት በኋላ ብሩክ ማርቆስ የጨረፋትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ባህርዳር ከተማዎችን መሪ ያደረገች ግብ ነች።
በጨዋታው ልዩነት ከፈጠረችው ግብ በኋላ
ቡድኖቹ በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ሲዘልቁ ከአስር ደቂቃዎች በኋላም የጣና ሞገዶች መሪነታቸውን ያጠናከረች ግብ አግኝተዋል። በጥሩ የቅብብል ሂደት በአደጋው ክልል ደርሳ በሂደቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ ያደረገው ተስፈኛው ሄኖክ ይበልጣል አመቻችቷት ግርማ ዲሳሳ በድንቅ ሁኔታ አክርሮ ያስቆጠራት ግብም የጣና ሞገዶቹን መሪነት ከፍ ያደረገች ግብ ነች።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው በመቅረብ አራት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ያደረጉት መቻሎች
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጫና ፈጥረው ከተጫወቱ በኋላ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። መሐመድ አበራ በቀኝ መስመር በኩል የነበረው ቻላቸው መንበሩ ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራት ኳስም የግብ ልዩነቱን ያጠበበች ግብ ነች።
መቻሎች ከግቡ መቆጠር በኋላ በዩዳሄ ዳዊት አማካኝነት አቻ የሚሆኑበትን አጋጣሚ ፈጥረው የነበረ ቢሆንም ፔፔ ሰይዶ ኳሷን እንደምንም መልሷት ጨዋታው በጣና ሞገዶች 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም በግብ የቀረቡ ሙከራዎች መታጀብ አልቻለም።
ዐፄዎቹ በተጠባቂው ጨዋታ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ በማድረግ ረገድ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን ቃልኪዳን ዘላለም የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅሞ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለችን ኳስ ወደ ግብነት ከመቀየሩ በፊት ግብ ጠባቂው ወጥቶ ያዳናት ኳስም ለዐፄዎቹ አስቆጪ አጋጣሚ ነበረች።
በረዣዥም ኳሶች እንዲሁም በፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ቡናማዎቹም ሁለት አጋጣሚዎች ፈጥረው ነበር። ዘላለም አባተ ያደረጋት ዓላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ እንዲሁም በአጋማሹ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በፍቃዱ አለማየሁ መቷት በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣችው ኳስም የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ናቸው።

ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው የጨዋታ ምዕራፍ ሁሉ ቡድኖቹ በአመዛዡ ረዣዥም ኳሶችን በመጠቀም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር።
በጅማሮው ዐፄዎቹ በአንፃራዊነት የተሻለ የፊት መስመር እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም ቀድመው ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ቡናማዎቹ ናቸው።
62ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ ተሻምታ ራምኬል ጄምሰ በግንባሩ ከገጫት በኋላ ዋሳዋ ጂኦፍሪ በአግባቡ ያላራቃትን ኳስ ተጠቅሞ ዘላለም አባተ በአስደናቂ መንገድ ተገልብጦ ከመረብ ጋር ያዋሀዳት ድንቅ ግብም ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችላለች።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡናማዎቹ መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ዐፄዎቹ ደግሞ የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈት ላለማስተናገድ ብርቱ ፉክክር ያደረጉ ሲሆን በ74ኛው ደቂቃ ላይም አቡበከር አዳሙ ሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ ሁለት ተከላካዮች በማለፍ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹ መሪነታቸውን ማጠናከር ችለዋል።
እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ጫና ፈጥረው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት ዐፄዎቹም በያሬድ ብርሀኑ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታም ቡናማዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ድል ሲያደርጉ ዐፄዎቹ የዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናግደዋል።

