ወገኔ ገዛኸኝ የግብፅ ጉዞ በምን ሂደት ላይ ይገኛል?

ወገኔ ገዛኸኝ የግብፅ ጉዞ በምን ሂደት ላይ ይገኛል?

በቀዳሚነት ወገኔ ገዛኸኝ ወደ በግብፅ ሊያቀና እንደሆነ መዘገባችን ሲታወቅ አሁን የጉዞው ሁኔታ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ተጨማሪ መረጃ እናደርሳችኋለን።

በኢትዮጵያ መድን ከታችኛው ቡድን አንስቶ በዋናው ቡድን ያለፉትን አምስት ዓመታት እያገለገለ የሚገኘው አማካይ ወገኔ ገዛኸኝ የግብፅ ክለብ ሞካውሎን አል ዓረብ ስፖርት የሁለት ዓመት ተኩል ኮንትራት እንዳቀረበለት እና በቀናት ውስጥ ሊያቀና እንደሚችል አስቀድመን ከቀናት በፊት መረጃውን አድርሰን እንደነበር ይታወሳል።

በዚህ ጉዳይ ላይም ተጫዋቹ ከOBN ጋር ትናንት ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦለት “ዕድሉ መጥቶልኛል ከፈጣሪ ጋር ይሳካል ብዬ አስባለው። መቼ እንደምሄድ አልተረጋገጠም ፤ ብቻ የሚሆነውን እናያለን።” ሲል ወደ ግብፅ እንደሚሄድ አረጋግጧል።

በማስከተል የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቶላቸው ሲመልሱ “የወገኔ ጉዳይ ገና ነው ጥያቄ መጥቶለታል ከግብፁ አረብ ኮንትራክተር። ልጁ በእውነት ይገባዋል። ከዚህም በላይ መሄድ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ግን ክለቡ ነው የሚወስነው እኔ አይደለውም። የጠየቀው ክለብ በነፃ ዝውውር መውሰድ ነው የፈለገው ይሄ ነው ልዩነት ያለው። ክለቡ በነፃ እሰጣለሁ ካለ የምናየው ነው። ተስፋ አደርጋለሁ ልጁ ትልቅ ደረጃ ደርሶ እንደማይ” በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

በወገኔ ዝውውር ላይ እንከን ሆኖ የመጣው ፈላጊው የግብፅ ክለብ በነፃ ማዘዋወር መፈለጉ ሲሆን ይህን ደግሞ የተጫዋቹ ባለቤት ክለቡ የመጣለትን ዕድል ይቀበላል ወይስ እንዲቆይ ያደርገዋል የሚለው ተጠባቂ ነው።

ሶከር ኢትዮጵያ የወገኔ የዝውውር ሂደት አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ስትል ባደረገቸው ማጣራት የክለቡ የበላይ አካላት ዛሬ ወገኔን ጠርተው ለማናገር ቀጠሮ እንደ ያዙ እና እስከ አመሻሽ ድረስ ነገሮች ቁርጣቸው እንደሚታወቅ ሰምተናል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖር የተለየ ነገር ካለ የምናሳውቃችሁ ይሆናል።