17ኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚካሄዱ አራት ጨዋታዎች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ከበዓል ጋር በተያያዘ ምክንያት ከፋሲል ከነማ ጋር ሊያደርጉት የነበረውን የ16ኛ ሳምንት ጨዋታ ያላከናወኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሀያ ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በመጨረሻው ጨዋታ ከመመራት ተነስተው ሽረ ምድረ ገነትን ሦስት ለአንድ ያሸነፉት ነብሮቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ 3 ግቦች ባስቆጠሩበት መርሐግብር ላይ ያሳዩትን እንቅስቃሴ ማስቀጠል ቀዳሚ የቤት ሥራቸው ነው። ከዘጠኝ ቀናት በኋላ የሊግ ጨዋታ የሚያከናውነው ቡድኑ ዛሬ ድል ማድረግ የደረጃ መሻሻል ስለሚያስገኝለት ከወትሮ ለየት ባለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ ይቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።
በ13 ነጥቦች 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ነብሮቹን ይገጥማሉ። በ9ኛው ሳምንት በስምዖን ማሩ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካሸነፉ በኋላ ከድል ጋር የተራራቁት ወልዋሎዎች የደረጃ መሻሻል ለማግኘት ካለባቸው ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜ መላቀቅ ግድ ይላቸዋል። በመጨረሻዎቹ አምስት መርሐግብሮች ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከሽንፈት መራቁ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ዋነኛው ደካማ ጎኑ የነበረው የመከላከል ድክመት መቅረፉ እንደ አወንታ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመሩ ማሻሻል ይጠበቅበታል።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ዳግም ንጉሤ እና ኢዮብ ዓለማየሁ በቅጣት ምክንያት አይኖሩም። በወልዋሎዎች በኩል ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው ስምዖን ማሩ እና ያሬድ ከበደ በጉዳት እንዲሁም የአራት ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት ሰመረ ሀፍታይ በዛሬው ጨዋታ አይሳተፉም።
የተሰረዘው እና በሀዲያ ሆሳዕና አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የ2012 ውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር 2 ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል። በጨዋታዎቹም ሁለቱም በእኩሌታ ሦስት ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
አዳማ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ
በሀያ ስድስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት ያሳዩትን መሻሻል አስቀጥለው ደረጃቸውን ለማሻሻል ምዓም አናብስትን ይገጥማሉ።
አዳማ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሐግብሮች በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል፤ ከሁለት ለባዶ መመራት አገግመው ከመሪው ሲዳማ ቡና ነጥብ በተጋሩበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሦስት ለሁለት ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ ደግሞ ለዚህ ማሳያ ነው። በተለይም በ 14 ሳምንታት ጉዞ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ሳያስቆጥር ከዘለቀ በኋላ በተጠቀሱት ሁለት ጨዋታዎች 5 ግቦችን ያስቆጠረው የፊት መስመሩ የሚታይ መሻሻል አስመዝግቧል። ሆኖም በሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስተናገደው የኋላ መስመሩ ከተጋጣሚው የፊት መስመር ጥንካሬ አንፃር በዛሬው ዕለት ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል።
አሰልጣኝ ፀጋይ ኪዳነማርያምን ከቀጠሩ በኋላ ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች 3 ድል እና 3 የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች አስራ ሁለቱን ያሳኩት ምዓም አናብስት በአስራ ስድስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በመጨረሻው መርሐ ግብር ጠንካራውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ለአንድ አሸንፎ ወደ ዛሬው ጨዋታ የሚቀርበው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እያደረገው ያለውን ጉዞ ለማሳለጥ በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉበትን የግብ ዕድሎች የመፈፀም ድክመት መቅረፍ ይጠበቅበታል። ከዚህ በተጨማሪም ከመጨረሻዎቹ ስድስት መርሐ ግቦች ውስጥ በአራቱ መረቡን አስከብሮ ሁለት ግቦችን ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ማስቀጠል ከቡድኑ ይጠበቃል።
በአዳማ ከተማ በኩል በባለፈው ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የወጣው አህመድ ሁሴን እና ልምምድ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ነቢል ኑሪን ጨምሮ ማይክል ኪፕሩቪም በጉዳት ምክንያት የማይኖር ሲሆን አምበሉ ሐይደር ሸረፋ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ልምምድ ተመልሷል። ሆኖም ግን በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር ረፋድ ላይ የሚታወቅ ይሆናል። መቐለ 70 እንደርታዎች በበኩላቸው በዛሬው ጨዋታ ጉዳት ላይ ያሉት ሱሌይማን ሐሚድ፣ ዘርኢሰናይ ብርሀነ፣ አማኑኤል ልዑል እና ተመስገን ተስፋየ ግልጋሎት አያገኙም በመጨረሻው ጨዋታ በቤተሰብ ጉዳይ ከቡድኑ ጋር ያልነበረው መሐሪ አመሀ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ነው።
ቡድኖቹ 6 ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 70 እንደርታ 3 ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ አንዱን አሸንፎ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። መቐለ 8፣ አዳማ 5 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ አልተካተተም)
አርባምንጭ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በስምንት ነጥቦች ግርጌው ላይ የተቀመጡት አርባ ምንጭ ከተማዎች ከድል ጋር ዕርቀ ሰላም ሳያወርዱ 17ኛው ሳምንት ላይ ደርሰዋል። ከተከታታይ ሦስት የአቻ ውጤቶች በኋላ በመቻል እና በሽረ ምድረ ገነት ሽንፈት ያስተናገዱት አዞዎቹ
ካሉበት አስጊ ሁኔታ ለመላቀቅ ዘርፈ ብዙ ለውጦች
ማድረግ ግድ ይላቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻው መርሐ ግብር ላይ አንፃራዊ መሻሻል ማሳየት ቢችልም አሁንም ኳስና መረብ ሳያገናኝ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥሯል። ይህንን ተከትሎ አሰልጣኝ አበባው ቡጣቆ በ16 ሳምንታት ጉዞ 5 ግቦች ብቻ አስቆጥሮ 17 ግቦች ያስተናገደውን ቡድን የውድድር ዓመት ጉዞ ለማቃናት ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በጥምቀት በዓል ምክንያት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሊያደርጉት የነበረውን የ16ኛው ሳምንት ጨዋታ ያላከናወኑት ፋሲል ከነማዎች ወደ ሰንጠረዡ አናት የሚያስጠጋቸውን ድል ለማግኘት ከአዞዎቹ ጋር ይፋለማሉ።
በሀያ ስድስት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ዐፄዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አንድ ለባዶ ካሸነፉበት የ12ኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ድል ማድረግ አልቻሉም። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ከአዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ደግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል። በተጠቀሱት ሦስት መርሐ ግብሮች ላይ ግብ ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ በዛሬው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች በቂ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ችግሩን መቅረፍ ይጠበቅበታል።
አርባምንጭ ከተማዎች ጉዳት ላይ ያሉት በርናንድ ኦቼንግ እና ሳሙኤል አስፈሪን አያሰልፉም፤ ሆኖም ጉዳትና ቅጣት ላይ የነበሩት በፍቅር ግዛቸው እና ይገዙ ቦጋለ መመለሳቸው ለቡድኑ መልካም ዜና ነው። ፋሲል ከነማ በረከት ግዛው፣ አምሳሉ ጥላሁን እና አብዱልአዚዝ አማንን በጉዳት እንዲሁም አቤኔዘር ዮሐንስን በቅጣት በዛሬው ጨዋታ የማያገኙ ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪሚየር ሊጉ በአስር አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም በተመሳሳይ
በሦስት በሦስት ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገው
በተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ዐጼዎቹ 7 አዞዎቹ ደግሞ 6 ግቦች አስቆጥረዋል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
በ21 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች መልስ ድል አድርገው ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለማለት ከሐይቆቹ ጋር ይፋለማሉ።
ካከናወኗቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በዘጠኙ
ነጥብ የተጋሩት የጣና ሞገዶቹ በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ቀዳሚ ናቸው። ቡድኑ ከአራት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ በ14ኛው ሳምንት መቻልን ማሸነፍ ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ዳግም ወደ ነጥብ መጋራት ተመልሷል። ቡድኑ በሰባት ጨዋታዎች ከሽንፈት መራቁ እንዲሁም አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ በበጎነት የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም ከገጠሙት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ለመላቀቅ ግን በተጠቀሱት ሰባት መርሐ ግብሮች ውስጥ ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ጥርስ አልባው የፊት መስመሩ ማሻሻል ግድ ይለዋል።
ሀያ ስምንት ነጥቦችን ሰብስበው ከመሪው ሲዳማ ቡና በአምስት ነጥቦች ርቀው 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች መሪው በዕለተ ማክሰኞ ጨዋታውን ከማከናወኑ በፊት የነጥብ ልዩነቱን አጥብበው ጫና ለማሳደር ወሳኝ ድል ለመጎናፀፍ እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በመጨረሻው ጨዋታ የነገሌ አርሲን ግስጋሴ መግታት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች በዕለቱ ያሳዩት እንቅስቃሴ እና የማሸነፍ መንፈስ ምንያህል ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሆኑ ፍንጭ ያሳየ ነበር። በጨዋታው የተጋጣሚን ዋነኛ የማጥቂያ መንገድ በመግታት ረገድ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርገው በነበራቸው የመከላከል ጥንካሬ እና ዕድሎችን የመጠቀም ብቃት ለድል የበቁት ሐይቆቹ በዛሬው ዕለት በሰባት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል ውቅር ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው የፊት መስመር ጥንካሬያቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።
ባህር ዳር ከተማ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ክንዱ ባየልኝን በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄን ደግሞ በቅጣት ሲያጣ አምበሉ በረከት ጥጋቡ ግን ከቅጣት ይመለሳል። በሀዋሳ ከተማ በኩል አምበሉ ቢኒያም በላይ በጉዳት ምክንያት አይኖርም።
ባህር ዳር እና ሀዋሳ በሊጉ እስካሁን በ12 ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች እኩል አራት አራት ጊዜ አሸንፈው በአራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። በግንኙነቱ ሀዋሳ ከተማ 12፤ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ 11 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

