ሪፖርት| አዲስ አበባ የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

ሪፖርት| አዲስ አበባ የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

ኢትዮጵያ መድን እና ፋሲል ከነማ 0 ለ 0 ሲለያዩ የፈረሰኞቹን እና ቢጫ ለባሾቹ ጨዋታ 1ለ1 ተጠናቋል

ኢትዮጵያ መድን ከ ፋሲል ከነማ

 

የ19ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ቀዳሚው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ብዙም ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት ያልተደረገበት እንዲሁም ጥቂት የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። ኢትዮጵያ መድኖች በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ያሬድ ካሳዬ ከግራ መስመር አሻምቷት ሞየስ ፖዋቲ እንደምንም ካወጣት አጋጣሚ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ቀዝቃዛ ጅማሮ ካደረጉ በኋላ የኋላ ኋላ በመስመሮች በኩል ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ዐፄዎቹም በረከት ግዛው አሻግሮት ቃልኪዳን ዘላለም ባደረገው እና በረከት ግዛው ከሳጥን ውጭ ባደረገው ሙከራ የግብ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል።

የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ በማስመልከት በተመለሰው ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ መድኖች አንፃራዊ መሻሻል አሳይተው ከመጀመሪያ አጋማሽ በተሻለ መንገድ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል። ዒላማቸውን ባይጠብቁም የግብ አጋጣሚዎችን የፈጠሩት ዐፄዎቹ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ድረስ የግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉ ቢሆንም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።

 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልዋሎ ዓ/ ዩ

 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የጀመሩት ሲሆን በ13ኛው ደቂቃም ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሀብታሙ ጉልላት በረዥመ አሻግሮት የቢጫ ለባሾቹ ተከላካይ ወግአየሁ ቡርቃ ኳሱን ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ በሰራው ስህተት ፍፁም ጥላሁን አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ መሬት ለመሬት መትቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሆኖም ግን ፈረሰኞቹ በመሪነት የቆየው ለሦስት ደቂቃ ብቻ ነበር። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የተንቀሳቀሱት ቢጫ ለባሾቹ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ገብሩ ሳጥን ውስጥ ኳስ ሲያሻግር ኳሱ የፈረሰኞቹ ተጫዋች በሆነው ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል ላይ ተጨርፎ ወደ ግነብት ተቀይሮ አቻ መሆን ችለዋል። ከግቦቹ መቆጠር በኋላ ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ ሲሆኑ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር የቀረቡባቸው ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል። አቤል ያለው ከሳጥኑ ጠርዝ መቶት ግብ ጠባቂው እንደ ምንም ጨርፎ ያወጣው እንዲሁም ሀብታሙ ጉልላት ከሳጥን ውስጥ ሞክሮት ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ እና ተገኑ ተሾመ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ወልዋሎዎች ተሻሸለው የቀረቡበት ነበር። ቢጫዎቹ በጅማሮው በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል መድረስ ከቻሉ በኋላም በ57ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ዳዊት ገብሩ ላይ በተሰራ ጥፋት የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ቢችሉም ፍሬው ሰለሞን አጋጣሚውን ሳይጠቀም በመቅረቱ መሪ መሆን የሚችሉበትን ዕድል አባክነዋል።

በአጋማሹ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ የቆዩት ፈረሰኞቹ 78ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከሳጥኑ ጠርዝ መሬት ለመሬት መቶ ግብ ጠባቂው በመለሰበት እንዲሁም ቧይ ኮች ተጨራርፎ ካገኛት በኋላ በግሩም ሁኔታ መቷት በድጋሚ በግብ ጠባቂው በተመለሰች ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።