ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ነጥብ ሲጋሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጣፋጭ ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ነጥብ ሲጋሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጣፋጭ ድል ተቀዳጅተዋል

በድራማዊ ክስተቶች በታጀበው ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ 3-3 ሲለያዩ ቡናማዎቹ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ባለ ድል ሆነዋል

 

አዳማ ከተማ ከ ሸገር ከተማ

 

አዳማ ከተማዎች ብልጫ የወሰዱበት የመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን 10ኛው ደቂቃ ላይም አቡበከር ሳኒ ከሜዳው የአማካኝ ክፍል በመነሳት በጥሩ ሁኔታ ይዞት ገብቶ ያቀበለውን ኳስ አህመድ ሁሴን ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ሸገር ከተማዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ከሜዳው የመሃል ክፍል ላይ ናትናኤል ዘለቀ በጥሩ መንገድ ያቀበለውን ኳስ አዲሱ ፈራሚ ቢንያም ፍቅሩ ወደ ግብነት ቀይሮ በአዲሱ ክለቡ የግብ ካዝናውን ከፍቷል። መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ አምስት ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሸገር ከተሞች ከመመራት ተነስተው መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 87ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ ከገባ አንድ ደቂቃ ብቻ ሜዳ ላይ ያሳለፈው ጄቤሳ ሜኤሳ በመጀመሪያው የኳስ ከፍ በማድረግ ድንቅ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን በደስታ ማዕበል ማናወጥ ችሏል።

ሆኖም 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመሩ ስድስት ደቂቃዎች ውስጥ (90+1) ላይ በሜዳው የግራ ክፍል የአዳማ ከተማው ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አላዛር ሽመልስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ በማስቆጠር ሸገር ከተማዎች ያገኙትን ደስታ መንጠቅ ችሏል። ድራማዊ ክስተቶች በተበራከቱበት ጨዋታ የአቻነቱን ግብ ካስቆጠረ ከአራት ደቂቃ በኋላ 90+5 ላይ የግቡ ባለቤት ራሱ አላዛር ሽመልስ በግራ እግሩ ሳጥን ውስጥ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ መረብ ጋር በማገናኘት አዳማ ከተማዎችን በድጋሚ መሪ አድርጓል።

ነገር ግን አዳማ ከተማዎች ደስታቸው ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ መዝለቅ አልቻለም። የተሰጡት ጭማሪ ደቂቃዎች ተጠናቀው የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት የግቦቹ ባለቤት የሆነው አላዛር ሽመልስ በዮሴፍ ታረቀኝ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ሸገር ከተማዎች ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት 90+10 ላይ ሄኖክ አዱኛ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ በድራማዎች የታጀበው ጨዋታ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ቡድኖቹን ነጥብ አጋርቷል።

 

ነገሌ አርሲ ከ ኢትዮጵያ ቡና

 

ተመጣጣኝ የሚባል የኳስ ቁጥጥር በነበረበት ጨዋታ ወደ ግብ ተጠግቶ በመጫወቱ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን እነዚህን ኳሶች ወደ ግብ ሙከራ በመለወጥ ረገድ ሁለቱም ክፍተቶች ተስተውሎባቸዋል። በዚህም 43ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተሻግሮ የኢትዮጵያ ቡናው ኦካይ ጁል በግንባሩ ገጭቶ በግቡ ቋሚ ከወጣበት ሙከራ ውጪ ይሄ ነው የሚባል ሙከራን ሳያሳዩን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በፈጣን ሽግግሮች የታጀበ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ አስመልክተውናል። 70ኛው ደቂቃ ላይም የነገሌ አርሲው ዘሩባቤል ፈለቀ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳላንድ ኢብራሂም መልሶበታል።

87ኛው ደቂቃ ላይ የነገሌ አርሲው ተጫዋች ቦና ቦካ የግብ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጁ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ራምኬል ጄምስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ነገሌ አርሲዎች እጅጉን ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በተጨመሩ ደቂቃዎች ናትናኤል ሰለሞን ሞክሮት የግቡ ቋሚ በመለሰበት እንዲሁም ዲሴሬ ፓስካል በግንባሩ ገጭቶ በአግዳሚው በኩል በወጣበት ሙከራዎች ግብ ለማግኘት የጣሩ ሲሆን ነገር ግን ሳይሳካላቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።