አርባምንጭ ከተማ የቀድሞ ተጫዋቹን በድጋሚ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሷል

በአስራ ስድስት ነጥብ በሊጉ ግርጌ የተቀመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ቀደም ብለው የተከላካዩን ፀጋዬ አበራን ውል ለማራዘም ከስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዚህ በፊት በክለቡ ቆይታ የነበረው ናይጄርያዊው የተከላካይ አማካይ ቻርለስ ሪባኑ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል። ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በሀምበሪቾ፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ባህርዳር ከተማ፣ አዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች ዳግም ወደ አዞዎቹ ቤት ለመመለስ ከስምምነት መድረሱን ተከትሎ አንዳንድ የጉዞ ሁኔታዎች ካገባደደ በኋላ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ዝውውሩን ያጠናቅቃል ተብሎ ይጠበቃል።

