በ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የአዳማ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 3ለ1 በሆነ ውጤት ሲዳማ ቡና ላይ ድል ሲቀዳጅ መቻል ከ ወልዋሎ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወደ መሪዎቹ የሚጠጋበትን ዕድል አምክኗል

መቻል ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ቀዝቃዛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመቻል በኩል 28ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከሁለት ደቂቃዎች በኩል በወልዋሎ በኩል እንዳልካቸው ጥበቡ ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላ መቻሎች 37ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቸርነት ጉግሳ ከበረከት ደስታ በተሰነጠቀለት ኳስ ከፍ አድርጎ (ቺፕ) ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሙታክብዋ ጆኤል በግሩም ብቃት አድኖበታል።

ከዕረፍት መልስ መቻሎች በመጠኑ ተነቃቅተው ቀርበው 66ኛው ደቂቃ ላይ በኮሊንስ ኮፊ አማካኝነት ሙከራ ካደረጉ በኋላ 76ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት ወርቃማ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አብዱልከሪም በሳጥኑ የግራ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ ኪም ላም በሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቸርነት ጉግሳ መትቶት ሙታክብዋ ጆኤል አድኖበታል።
ወልዋሎዎች የጨዋታውን ብቸኛ ንጹህ የግብ ዕድላቸውን 82ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረው ዳዊት ገብሩ ከግራ መስመር የቀነሰለትን ኳስ ያገኘው ሰመረ ሀፍተይ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
መቻሎች በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ 90+7′ ላይ የመጨረሻውን የግብ ዕድል ፈጥረው መሐመድ አበራ የቀነሰለትን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ተክሉ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ሙታክብዋ እና በግቡ የግራ ቋሚ ተመልሶበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።
ወላይታ ድቻ ከ ሲዳማ ቡና
በሳምንቱ እጅግ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲዳማዎች ሲያደርጉ አስቻለው ሙሴ ከርቀት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ካዲማ ዲያየ በቀላሉ ይዞበታል።
28ኛው ደቂቃ ላይ ድቻዎች ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሙሉቀን አዲሱ ከግራ መስመር ከርቀት ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ኪዳኔ አሰፋ የግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት በግንባሩ በመግጨት ኳሱን ማስቆጠር ችሏል።
በግለት ጨዋታውን ያስቀጠሉት የጦና ንቦች በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሲችሉ ከማዕዘን ተሻምቶ የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ሙሉቀን አዲሱ እንደመጀመሪያው ግብ በተመሳሳይ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መልካሙ ቦጋለ በግንባር በመግጨት ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ይህ ግብ ሲቆጠርም ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ተመሳሳይ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ሠርቷል።

ከዕረፍት መልስ ሲዳማዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ከቀሩ ከሴኮንዶች በኋላ ሦስተኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። ሳሊፉ ኢብራሂም ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ያሬድ ዳርዛ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ አክርሮ የመታው እጅግ አስደናቂ ኳስ መረቡ ላይ አርፏል። ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ወላይታዎች 69ኛው ደቂቃ ላይ አራተኛ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሙሉቀን አዲሱ የሰነጠቀለትን ኳስ ያገኘው ቅዱስ ቂርቆስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ካል መልሶበታል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ሲዳማዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ በቡድኑ ማልያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው አቤል ያለው አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ለዜሮ ከመሸነፍ ድነዋል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

